ፖለቲካ
የአንካራው ስምምነት አለመግባባትን በመፍታት ትብብርን ማጎልበት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው - የሶማሊያ አምባሳደር አብዲረሽድ ሴድ
Feb 14, 2025 29
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፦ የአንካራው ስምምነት ጎረቤት ሀገራት አለመግባባትን በዲፕሎሚሲያዊ መንገድ በመፍታት ትብብርን ማጎልበትና ለቀጣናው አንድነትና ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የሶማሊያ መንግስት አምባሳደር አብዲረሽድ ሴድ ገለጹ። ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ አንድነት፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በማጎልበት ለቀጣናዊ ትስስር ወሳኝ እርምጃ እንደሆነም ተናግረዋል። በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልዩ ተልዕኮ ዲፕሎማት የሆኑት አምባሳደር አብዱረሺድ ሴድ፤ የአንካራው ስምምነት ለቀጣናው ሁሉን አቀፍ ትብብርና ሰላም መጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። ስምምነቱ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ዘላቂ ሰላምና ብልፅግናን ለማምጣት የዲፕሎማሲ አማራጭ ያለውን ሚና በተመለከተ ማሳያ እንደሆነ አስረድተዋል። ታሪክና ባህል ያስተሳሰራቸው ሁለቱ ሀገራት ለጋራ ፈተናዎቻቸው ቅድሚያ በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ስምምነቱ በር ከፋች እንደሆነም ጠቁመዋል። የአንካራ ስምምነት ሀገራት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲችሉ ምቹ ከባቢ ፈጥሯል ያሉች አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት የምትጫወተውን ወሳኝ ሚናም አንስተዋል። የሀገራት ቁጭ ብሎ መነጋገር ለጋራ ብልፅግና እና የህዝቦች ተጠቃሚነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የአንካራው ስምምነት ትልቅ ምሳሌ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ክብሯን የሚመጥንና ገፅታዋን የሚገነባ ዝግጅት በማድረግ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
Feb 14, 2025 47
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ክብሯን የሚመጥንና ገፅታዋን የሚገነባ ዝግጅት በማድረግ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የጉባኤውን ዝግጅት፣ መስተንግዶ እና ለእንግዶች እየተደረገ ባለው አቀባበል ዙሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ ሀገራዊ ክብሯን በሚመጥን ደረጃ ዝግጅት አድርጋ የጉባኤ ተሳታፊዎችን በመቀበል ላይ ትገኛለች ብለዋል። ባለፈው ዓመት ለህብረቱ ጉባኤ ሀያ አምስት መሪዎች እንደመጡ በማስታወስ በዘንድሮው ጉባዔ የሚሳተፉ መሪዎች ቁጥር ሰላሳ አምስት መሆኑን ተናግረዋል። ለተሳታፊ እንግዶች ከኤርፖርት ጀምሮ መልካም አቀባበል በማድረግ በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታ አስደሳች እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ጉባኤው ኢትዮጵያ ክብሯን የምትገልፅበት እና ገፅታዋን ለዓለም የምታሳይበት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ሊመጥን የሚችል አቅርቦቶች ተሟልተው እንግዶች በመስተናገድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ለዘንድሮ ጉባኤ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለአንድ ዓመት ያህል ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው የአዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ የተከናወኑት ተግባራት ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል። በተሳታፊ እንግዶች ዘንድ የአዲስ አበባ ለውጥ መደነቅን የፈጠረ እንደሆነ ያነሱት አምባሳደር ብርቱካን ይህም የከተማዋን የዲፕሎማሲ መዲናነት የሚያፀና ነው ብለዋል። ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ቀደም ሲል ከአርባ በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በመዲናዋ መዘጋጀታቸውን አስታውሰው በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰሩ ያሉ የከተማ ማስዋብ ስራዎች የኮንፍረንስ ቱሪዝም ፍሰትን እንደሚያሳድግ መናገራቸው በመረጃው ተመላክቷል።
በፓርቲው የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን በክልሉ ለመፈጸም በላቀ ቁርጠኝነት ይሰራል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)
Feb 14, 2025 39
ቦንጋ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- በብልጽግና ፓርቲ የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን በክልሉ ለመፈጸም በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ። በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የክልሉ አመራር የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።   በመድረኩ ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በፓርቲው ሁለተኛ ጉባኤ የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች የክልሉን እና የህዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መፍታት ስለሚያስችሉ በላቀ ቁርጠኝነት ለመፈጸም እንደሚሰራ ገልጸዋል። ለዚህም አመራሩና አባሉ ከተለመደው አሰራር ወጥቶ በተጨባጭ ለውጥ በሚያመጣና ውጤትን መሰረት ባደረገ መልኩ የህብረተሰቡን ሕይወት የሚቀይር ተግባር ለመፈፀም መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል። በአንደኛው የፓርቲው ጉባኤ በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት በተከናወኑ ሥራዎች በክልሉ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በመሠረተ ልማት ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መግኘታቸውን ገልጸው ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል አመራሩ የበኩሉን እንዲወጣ አስገንዝበዋል። በጉባኤው በኢንቨስትመንት፣ በግብርና ልማት፣ በሰላም፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፍትሕ፣ በቴክኖሎጅና ሌሎች ዘርፎች የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ስኬታማ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።   እያንዳንዱ አመራር ቃልን በተግባር በመቀየር በህዝቦች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ባመጣው ልክ መገምገም እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው። የሥራ ባህልን በመቀየር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ ጠንካራ ድጋፍ ማድረግና ችግሮችን በጥልቀት ገምግሞ መፍታት ላይ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል። አሰባሳቢና የጋራ ገዥ ትርክት በሕዝቡ ዘንድ እንዲሠርጽና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።   ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የክልሉ አኖቬሽንና እንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ በሰጡት አስተያየት በፓርቲው ለተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ውጤታማነት ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።   የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በበኩላቸው ፓርቲው ያስቀመጠውን አቅጣጫና ውሳኔን መሰረት በማድረግና የክልሉን የመልማት አቅም በመጠቀም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት እንደምሰሩ ገልጸዋል። በመድረኩ አመራሩ የአመለካከትና የአስተሳሰብ አንድነትን ከመፍጠር ባለፈ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ በቅንጅት ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል። የብልጽግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎቸና አቅጣጫዎች ማሳለፉ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በልማት የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ እንደምታሳካ ጠንካራ እምነት አለን- አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
Feb 14, 2025 39
አዲስ አበባ፤የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በልማት የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ እንደምታሳካ ጠንካራ እምነት አለን ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ። ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፥ በውይይታቸው የድርጅቱና የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ትብብር ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በልማት እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ መገንዘባቸውን ጠቅሰው፥ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሎችን በማሳየት የከፍታ ጉዞዋን እንደምታሳካ ጠንካራ እምነት አለን ብለዋል። ኢትዮጵያ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል። ለቀጣናው ሰላምና ልማት እያበረከተች ያለውን ጉልህ ሚናም አድንቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር እና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የትብብር ጉዳዮች ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።
የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል
Feb 14, 2025 40
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የአልጄሪያ ፕሬዝደንት እና የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ሰብሳቢ አበዱልመጅድ ተቡን ገለጹ። የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት የአፍሪካ አገራት አጀንዳ 2063ን ከማስፈጸም አንጻር በኢኮኖሚ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያከናወኑት ስራ የሚገመገምበት መድረክ ነው። የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት 3ኛ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ እና 34ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።   ስርአቱ በመድረኩ የተገመገሙ አገራትን ሪፖርት አድምጦ አጽድቋል። እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት ለመገምገም ያመለከቱ አገራትን ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን በተጨማሪም የአቻ መገማገሚያ ስርአት መድረኩን የአንድ አመት የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት አጽድቋል። የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ሰብሳቢ አብዱልመጅድ ተቡን በዚሁ ወቅት ስርአቱ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት አስፈላጊ መሳሪያ ነው ብለዋል። የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር ጠቃሚ ዘዴ እንደሆነ በማስታወቅ አባል ሀገራት በፈቃደኝነት ለዚህ ስርአት መዋጮ በመክፈል ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡   የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት በበኩላቸው የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ስኬት የሚጀምረው ከ20 ዓመታት በፊት ከተደረሰው ስምምነት አንስቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአቻ ግምገማው የመሳተፍ የአገራት ፍላጎት እየተጠናከረ መምጣቱንና ተቋማዊ መሆኑን በመጥቀስ ስርአቱ በፈቃደኝነት ለሚገመገሙ አገራት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።   የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት በአህጉሪቱ የመንግስት አስተዳደርን ለማሻሻል ወሳኝ መሣሪያ ነው ያሉት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ናቸው። በአህጉሪቱ ሰላም፣ ብልጽግና እና ውህደትን ለመፍጠር ወሳኝ ዘዴ መሆኑን ገልጸው የአጀንዳ 2063 ራእይን ለማስፈጸም ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሊቢያ መንግስትና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብሔራዊ የሰላምና እርቅ ስምምነት ተፈረመ
Feb 14, 2025 40
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- የሊቢያ መንግስትና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብሔራዊ የሰላምና እርቅ ስምምነት ተፈርሟል። ስምምነቱን የአፍሪካ ህብረትና አደራዳሪ ኮሚቴው እንዳስፈጸሙት ተገልጿል፡፡ በዚሁ ወቅት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት ባስተላለፉት መልዕክት አፍሪካን ከሰላም እጦት ለማላቀቅ ህብረቱ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በተለይም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው እሳቤ የውስጥ ችግሮችን መፍታት አንዱና ዋነኛው ግብ መሆኑንም አብራርተዋል።   ሊቢያን ወደ ቀደመ ሰላሟ ለመመለስና የዜጎቿን ደህንነት ለማረጋገጥ የአፍሪካ ህብረት አስማሚ ኮሚቴ አቋቁሞ የማወያየት ስራ ሲያከናወን መቆየቱን አስታውቀዋል። ኮሚቴው ያቀረበው የስምምነት ሰነድ ሁለቱንም አካላት በፍትሃዊነት የዳኘና ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል። ለስምምነቱ ተፈፃሚነት የሊቢያ መንግስትም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ላይ የሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በስምምነቱ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በሱዳን ላለው ሰብዓዊ ቀውስ መፍትሔ ለመስጠት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር ይፈልጋል - ሼህ ሻክቦት አልናህያን
Feb 14, 2025 41
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- በሱዳን ላለው ሰብዓዊ ቀውስ መፍትሔ ለመስጠት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር ይፈልጋል ሲሉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቦት ቢን ናህያን አልናህያን ተናገሩ፡፡ በሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመክረው የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።   በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቦት ቢን ናህያን አልናህያን፣ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቦት ቢን ናህያን አልናህያን፤ ሀገራቸው ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በችግር ውስጥ የሚገኙ ሱዳናውያንን ለማገዝ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።   የዛሬው መድረክም የዚሁ ማሳያ መሆኑን አንስተው፤ መድረኩ ሱዳን ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ መካሄዱም ልዩ ትርጉም እንዳለው አንስተዋል። የምህረትና የፍቅር ምልክት የሆነው ታላቁ የረመዳን ወር ጥቂት ቀናት እንደቀሩት አንስተው፤ የረመዳን ወር በችግር ውስጥ የሚገኙ ሱዳናውያን ለመድረስ መልካም እድል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሱዳን ያለው አሁናዊ የሰብዓዊ ቀውስ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚፈልግም ነው ያብራሩት። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በ2023 በሱዳንና በአጎራባች ሀገራት ተጠልለው ለሚገኙ ሱዳናውያን 400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰው፤ አሁን ደግሞ 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አብራርተዋል። በሱዳን ከሚገኙ ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም