የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር ባለመለወጣቸው የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ልክ ማረጋገጥ አልተቻለም…ምሁራን

4108

ደሴ ሚያዝ 28/2010 ከፍተኛ ሃብት ፈሶባቸው የተሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር ባለመለወጣቸው የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ልክ ማረጋገጥም ሆነ  የሕብረተሰቡን ችግር መፍታት አለመቻሉን ምሁራን ገለጹ፡፡

ሰባተኛው አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው ትናንት ሲከፈት እንደተገለጸው ብዙ ወጪ፣ ጊዜና እውቀት የወጣባቸው የምርምር ሥራዎች ተግባር ላይ እንዲውሉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት በኃላፊነነት መስራት ያስፈልጋል፡፡በጉባኤው ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፐሮፌሰር ያለው እንዳወቅ እንዳሉት እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ምሁራን በትምህርት ጥራት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ቢያደርጉም ጥናቶቹ ወደ ተግባር አልተለወጡም።

በእዚህም በዘርፉ የሚፈለገውን ጥራት ለማረጋገጥ አለመቻሉን ነው የገሉጹት፡፡

“በምሁራን የሚወጡ የምርምር ስራዎች የህዝብን ችግር የሚፈቱና ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ የፖለቲካ አመራሩ በምርምር ሥራዎች ላይ በቂ ግንዛቤ ያለውና ለተግባራዊነታቸው ቁርጠኛ አቋም ያለው ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በምሁራኑና በፖለቲካ አመራሩ መካከል ያለውን ክፍተት በመሙላት ለጋራ አገራዊ ስኬትና የህዝቦች ተጠቃሚነት መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የማሕበረሰብ አገልግሎትና ስልጠና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ጉግሳ በበኩላቸው ጉባኤው በተለያዩ ምሁራን የተደረጉ ጥናቶች  ለሕዝብ ጥቅም እንዴት መዋል እንዳለባቸው ምክረ ሃሳብ ለማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡

በጉባኤው ላይ 47 የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ዶክተር ጌታቸው አስታውቀዋል፡፡

“በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በርካታ የምርምር ሥራዎች ቢሰሩም ከመደርደሪያ አልፈው የሕብረተሰቡን ሕይወት በተግባር ሲቀይሩ አይታዩም” ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናት፣ ምርምርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ ናቸው፡፡

“ምርምሮች ወደ ተግባር የሚለወጡበት ዕድል ከተፈጠረ የሕብረተሰቡን ሕይወት በተጨባጭ የመለወጥ አቅም አላቸው” ያሉት ዶክተር አልማዝ፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በደቡብ ክልል ሲዳማ አካባቢ የሚኖሩ ቡና አምራች ገበሬዎች ያጋጠማቸውን ችግር በመቅረፍ ያደረጉትን ጥረት ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ምርምሮች ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ማበርከት እንዳለባቸው ጥሪ እቅርበዋል፡፡

“ምርምር ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው አገር አቀፍ ጉባኤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና አራት የምርምር ተቋማት ታሳታፊ ሆነዋል፡፡