የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከንፋስ የሚመነጨውን ኃይል ወደ 504 ሜጋ ዋት ከፍ ያደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከንፋስ የሚመነጨውን ኃይል ወደ 504 ሜጋ ዋት ከፍ ያደርገዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፡- በአርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ የሚገኙ አራት ቀበሌዎችን የሚያካልለው አሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር ከንፋስ የሚመነጨውን ኃይል ወደ 504 ሜጋ ዋት እንደሚያሳድገው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።
የግንባታ አፈጻጸሙ 93 በመቶ የደረሰው ይህ ፕሮጀክት ካሉት 29 ተርባይኖች መካከል 23ቱ ተፈትሸው ከግሪድ ጋር መገናኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት ዐቅም እንዳለውም ጨምረው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል እየተገነባ የሚገኘው አይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ አፈጻጸም 85 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ካለው እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 48 ተርባይኖች መካከል 32 ተርባይኖች ተጠናቅቀው 80 ሜጋ ዋት እያመነጩ ይገኛሉ ብለዋል።
ቀሪዎቹን 40 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 16 ተርባይኖች ለመትከል አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የማምረት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ግንባታው ሲጠናቀቅም 120 ሜጋ ዋት የማመንጨት ዐቅም እንዳለው ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በቀጣይም የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን ለማስፋፋትና የኃይል ማመንጨት ስብጥሩን ለማመጣጠን በስምንት የተለያዩ አካባቢዎች መረጃ የመሰብሰብ ሥራ መሰራቱን አመልክተዋል።
በተሰበሰበው መረጃ መሰረትም የፕሮጀክት አዋጭነት ጥናት እና ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት በላይ ከንፋስ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ ሀብት መኖሩን በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ውጤቶች ማመልከታቸውንም ተናግረዋል።