የአፍሪካ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራምን በቁርጠኝነት ሊተገብሩ ይገባል- የአፍሪካ ህብረት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራምን በቁርጠኝነት ሊተገብሩ ይገባል- የአፍሪካ ህብረት

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 8/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) አፈጻጸም ውጤታማነት ለማሳደግ በትኩረት እንዲሰሩ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ።
ስድስተኛው የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ መደበኛ ስብስባ ከጥቅምት 11 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
በስብሰባው ላይ ሚኒስትሮች፣ ባለሙያዎች እና የልማት አጋሮች ይሳተፋሉ።
የአፍሪካ የግብርና ኢኒሼቲቮች አፈጻጸም መገምገም እና ዘርፉ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከር የስብሰባው አላማ ነው።
እ.አ.አ በ2023 በአዲስ አበባ የተካሄደውን አምስተኛው የልዩ ኮሚቴ ስብሰባ ውጤቶች ግምገማ ይደረጋል።
የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) የማላቦ ድንጋጌ (ከእ.አ.አ 2014 እስከ 2025) ስኬቶች እና የካዳፕ የካምፓላ ድንጋጌ (ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2035) አፈጻጸም ላይ ውይይት ይካሄዳል።
የስርዓተ ምግብን ማጠናከር፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ምርታማነት ስርዓት መዘርጋት፣ የበካይ ጋዞችን ልህቀት መቀነስ እና ዘላቂ የውሃና ተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደርን ማጠናከር ሌሎች የምክክር አጀንዳዎች ናቸው።
በአፍሪካ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ዘላቂ እድገትን ማምጣት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክረ ሀሳቦች ይቀርባሉ።
ውይይቱ እ.አ.አ በ2026 በአዲስ አበባ የሚካሄዱትን የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባና የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚሆኑ አጀንዳዎችን እንደሚያዘጋጅ ተመላክቷል።
የአፍሪካ ህብረት ግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር አጀንዳ 2063 ለማሳካት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ዘርፎች መሆናቸውን አመልክቷል።
ህብረቱ የግብርና እና የገጠር ልማት የበለጠ ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክቷል።
የህብረቱ አባል ሀገራት የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራምን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርቧል።
ስድስተኛው የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ጥቅምት 11 እና 12 እንዲሁም ጥቅምት 14 በሚኒስትሮች ደረጃ እንደሚከናውን ኢዜአ ከህብረቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።