ቀጥታ፡

የአፍሪካ መምህራን፤ የአህጉሪቷ መጻኢ ጊዜ ቀራጺዎች

አፍሪካ በወጣቶች የታደለች ሀገር ናት። 

ከአህጉሪቷ ህዝብ መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው እድሜው ከ25 ዓመት በታች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የአፍሪካ መጻኢ ጊዜን የሚወስነውን ወጣት ማን ያስተምረዋል? የሚለው ጥያቄ ቁልፍ ነው።

ይህ ጥያቄ ከመማሪያ ክፍሎች እና መጻሕፍት ባለፈ የአፍሪካ ልማት አበይት አጀንዳ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

በዓለም ደረጃ ትልቅ የእድገት እና የልማት ሞተር የሆነውን ወጣት በብዛት የያዘችው አፍሪካ ትውልዱን የሚቀርጽ መምህራን ውጪ ህልሟን ማሳካት የሚታሰብ አይሆንም።

የአፍሪካ ህብረት በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እ.አ.አ በ2030 በትንሹ 15 ሚሊዮን አዲስ መምህራን እንደሚያስፈልጉ አስታውቋል።

ይህን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እና ጠንካራ ሪፎርሞችን ማድረግ ይጠይቃል።

አፍሪካ የትምህርት መሰረተ ልማትን ለማሻሻል፣ የመምህራንን ቁጥር ለመጨመር እና በትምህርት ዘርፍ የተቀመጡ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት 90 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ሲል ህብረቱ ገልጿል። 

ጉዳዩ ከትምህርት ባለፈ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ያለው ነው። 

መምህራን የእያንዳንዱ ክህሎት፣ ስራ እና ኢኖቬሽን የሀሳብ መሐንዲስ ናቸው። የአፍሪካ መጻኢ ጊዜ የመወሰን አቅም አላቸው።

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የመምህራን ትምህርት ስርዓታቸው ላይ ማሻሻያ እያደረጉ ይገኛል።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፉ በርካታ ሪፎርሞችን እያደረገች ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንዱ የመምህራንን አቅም መገንባት እና የብቃት ደረጃን ማሳደግ ይገኝበታል።

የትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ የመምህራን ልማት ንቅናቄ በማድረግ መምህራን በተለያዩ የትምህርት እርከኖች አቅማቸውን እንዲጎለብት ተከታታይ ስልጠና እንዲያገኙ እያደረገ ነው። 

በአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም አማካኝነንት ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ መምህራን የዲጂታል ክህሎታቸው በማዳበር እና ተከታታይ የብቃት ምዘና በማድረግ አቅማቸውን እየተገነባ ይገኛል።

በነዚህ ስራዎች የትምህርት ውጤት ላይ አበረታች መሻሻሎች ታይተዋል።  መንግስት የሰለጠነ መምህራንን ቁጥር ማሳደግን የሪፎርሙ አካል አድርጎ እየሰራ ነው።  

ጋና የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችን ወደ ዩኒቨርስቲ በማሳደግ ሙያዊ ልህቀትን ለማረጋገጥ እየሰራች ትገኛለች።

ኬንያ ብቃት ላይ የተመሰረተ የስርዓተ ትምህርት ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ የመምህራን መማር ማስተማር የበለጠ ተግባር ተኮር እና ተማሪዎችን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን የጀመረችው ተግባር ተጠቃሽ ነው።

ሩዋንዳ የስርዓተ ትምህርት አሰራሮቿን ከመምህራን ስልጠና ጋር በማጎዳኘት የመምህራን እጥረትን ለመቀነስ እና ክህሎታቸውን ለማሳደግ እየሰራች ነው።

ለትምህርት ዘርፍ የሚመደበው በጀት በቂ አለመሆን፣ የተማሪ እና ክፍል ጥምርታ አለመመጣጠን፣ የዩኒቨርሲቲ እና ኢንዱስትሪ ትስስር በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ፣ የዲጂታል ክህሎት ማነስ እና ከፍላጎት አንጻር በቂ የሰለጠነ መምህራን አለመኖር የአህጉሪቷ የትምህርት ዘርፍ ፈተናዎች ናቸው።

የፓን አፍሪካ የመምህራን ትምህርት ኮንፍረንስ በያዝነው ሳምንት በአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ተካሄዷል።

"በአፍሪካ የመምህራን ትምህርት ስርዓትን መቀየር” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ኮንፍረንስ የትምህርት ሚኒስትሮች፣ የመምህራን ማህበራት ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የግሉ ዘርፍና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በኮንፍረንሱ ላይ ባደረጉት ንግግር ትምህርት ለሰው ሃብት ልማትና ለምጣኔ ሀብት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

በአፍሪካ የሚፈለገውን ልማትና ዕድገት ለማምጣት የትምህርት ተደራሽነት ላይ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሪፎርሞችን ተግባራዊ ማድረጓንና በዚህም ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።

የመምህራንን አቅም ለመገንባት የተለያዩ ስልጠናዎች በመስጠት በኩልም የተሻለ ስራ መሰራቱን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የጠቀሱት።

የትምህርት ጥራትና የመምህራን እጥረት ላይ እንደ አህጉር አሁንም ያልተፈታ ችግር መኖሩን ጠቁመው፤ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አባል ሀገራቱ ትብብራቸውን የበለጠ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የትምህርት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ጋስፓርድ ባንያንኪምቦና በበኩላቸው በአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባትና ሳይንስና ፈጠራን የበለጠ ለማዳበር የመምህራንን አቅም ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለዚህም ለመምህራን አቅም ግንባታ የተለያዩ ኤኒሼቲቮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ የ2063 የልማት ዕቅዶች ዕውቀት መር በሆነ መንገድ ቢተገበሩ ውጤታማ ይሆናሉ ብለዋል።

የአፍሪካ መምህራንን አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፈጣንና ተለዋዋጭ ቴክኖሎጂ ጋር መላመድ እንደሚገባም ነው ያነሱት።

በአፍሪካ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን የበለጠ ለማሳደግ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከወቅቱ ጋር ማዛመድ ይገባል ብለዋል።

በኮንፍረንሱ ላይ መምህራንንና ትምህርትን የተመለከቱ የተለያዩ አህጉራዊ ስትራቴጂዎች ይፋ ተደርገዋል።

  • የአፍሪካ የትምህርት ስትራቴጂ (ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2035 የሚተገበር)
  •  የአፍሪካ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ፣ የአፍሪካ ሳይንስ
  •   ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ስትራቴጂ  እንዲሁም የአፍሪካ የትምህርት 
  •   የክህሎት ልማት የድርጊት መርሃ ግብር ይፋ ሆነዋል። 

በተጨማሪም የአፍሪካ መምህራትን ማህበረሰብ የአሰራር ማዕቀፍ ወደ ትግበራ ገብቷል።

ይፋ የሆኑት ስትራቴጂዎች እና የአሰራር ማዕቀፎች የመምህራን ትምህርት፣ ሙያዊ ልህቀት፣ መሰረተ ትምህርት፣ ዲጂታል ክህሎቶች እና ኢኖቬሽን ተኮር የማስተማር ዘዴ ላይ መዋቅራዊ ለውጦችን የማምጣት ግብ እንዳላቸው የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል። 

በኮንፍረንሱ ላይ የ2025 የአፍሪካ መምህራን ሽልማት የተካሄደ ሲሆን የዘንድሮው የዓለም የመምህራን ቀን በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል።

አህጉራዊው ሁነት በአፍሪካ የመምህራን ድምጽ የበለጠ ጎልቶ እንዲሰማ የማድረግ ፣ የትምህርት ኢንቨስትመንት መጠን እንዲያድግ እና የባለድርሻ አካላት ትብብርን የማጠናከር አላማ እንዳለው ተገልጿል።  

የመምህራንን አቅም ማሳደግ የአፍሪካ የትምህርት ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ አበይት ትኩረቶች መካከል አንደኛው መሆኑን ህብረቱ በመረጃው አመልክቷል።

ህብረቱ እ.አ.አ 2024 የትምህርት ዓመት ብሎ በመሰየም የሰጠው ስትራቴጂካዊ ትኩረት የዚሁ ማሳያ ነው። የፓን አፍሪካ ኮንፍረንሱ የመምህራን ትምህርት የአፍሪካ የልማት አጀንዳ አበይት ትኩረት መሆኑ በግልጽ ታይቶበታል። 

የመምህራንን እጥረትን መቀነስ ብዙ መምህራንን ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን ስልጠና ጥራት ያለው፣ ነባራዊ እውነታን ያገነዘበ እና መጻኢውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል።

የአፍሪካ መንግስታት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች የመምህራን ትምህርት ስርዓትን መቀየር ትኩረታቸውን ባደረጉበት በአሁኑ ወቅት የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ የቀና የሚያደርገውን አፍሪካዊ ማን ያስተምራል? የሚለው ጥያቄ ተስፋ የሚሰጥ ምላሽ ያገኛል። 

የሰለጠነ፣ በክህሎት የዳበረ እና የኢኖሼሽን እውቀቱ ያደገ መምህር ለአፍሪካ ቀጣይ ጉዞ መቀናት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም