ቀጥታ፡

  "ያሆዴ"- ከተናጠል ይልቅ በትብብር የመድመቅ ተምሳሌት

   (በማሙሽ ጋረደው - ከኢዜአ ሆሳዕና ቅርንጫፍ)

የሀዲያ የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው "ያሆዴ" የማህበራዊ መስተጋብር መሰረት ነው። ለማህበራዊ የህይወት አመራር ጉልህ አስተዋጾም ስላለውም በሀዲያዎች ዘንድ በየዓመቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይከበራል፡፡ "ያሆዴ" ያለፈውን አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲስ ዘመን የሚቀበሉበት፤ የመጻኢ ተስፋ ብስራትና የልምላሜ ምልክትም ጭምር ተደርጎም ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም በዓሉ ሲቀርብ የሀዲያ ተወላጆችና የበዓሉ ተሳታፊዎች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ከያሉበት ወደአካባቢው በመምጣት ይሰባሰባሉ፡፡ በዘንድሮ የያሆዴ በዓልም የሀድያ ተወላጆች የተለያዩ ማህራዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን ለመከወን እንዲመች ታስቦ በተዘጋጀ ስፍራ (ነፈራ) ተሰባስበው በዓሉን በድምቀት  አክብረውታል፡፡

በበዓሉ አከባበር ያለፈው ዓመት ስኬትም ይገመገማል፤ በአዲሱ ዓመትም የተሻለ ተሰርቶ ስኬት እንዲመዘገብ በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ይካሄዳል። ሊተገበር የሚችል ዕቅድም ይታቀዳል፡፡ በግልና በቤተሰብ የመጡ ስኬቶች በጋራ በመሆን ይገመገማሉ። የበረቱና ውጤት ያስመዘገቡም እንዲበረታቱ ይደረጋል። ለዚህም ነው "ያሆዴ" የማህበራዊ መስተጋብር መሰረት ነው የሚባለው። ሰዎች እንዲሰሩና ስኬት እንዲያስመዘግቡ የሚያበረታታ እሴት አለው። 

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፋን ቦጋለ እንደሚሉት የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል "ያሆዴ" ከተናጠል ይልቅ በትብብር የመድመቅ ተምሳሌት ነው፡፡ ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የበዓሉ መቃረብን የሚያበስሩት ታዳጊ ልጆች ናቸው። ልጆቹ የዋሽንት (ገምባቡያ) ድምጽ ማሰማት ከጀመሩ በጉጉት የሚጠበቀውን የዘመን መለወጫ "ያሆዴ" በዓል መድረሱ ምልክት ነው።

በዓሉ ሀድያዎች አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት የሚጀምሩበት ወቅት ነው። በዓሉ የብሩህ ተስፋ፣ የሠላም፣ የፍቅር፣ የረድኤት፣ የበረከት ተምሳሌት በመሆኑም የተለየ ትርጉምና ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች ተራርቀው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ከያሉበት ይሰባሰባሉ። በዓሉ በአማረ መልኩ እንዲከበርም ሁሉም የቤተሰብ አባላት የየራሳቸው የሥራ ድርሻቸውን ያከናውናሉ። 


 

አባውራዎች ለበዓሉ ሠንጋ መግዣ የሚሆን ገንዘብ በቱታ ወይም በቅርጫ ቡድናቸው አማካኝነት እየቆጠቡ ይቆያሉ። እንዲሁም ለእንስሳት የሚሆን የግጦሽ ሳር የሚያበቅል ቦታ ከልለው ያዘጋጃሉ፡፡ ይህ የሚሆነበት ምክንያት ደግሞ በዓሉ በሚከበርበት ሰሞን የሰው ልጅ ይቅርና እንስሳትም መጥገብ አለባቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡

እማውራዎች ከበዓሉ ሦስትና አራት ወራት አስቀድመው እንሰት በመፋቅ ቆጮና ቡላ ያዘጋጃሉ። በተጨማሪም ከአካባቢው እናቶች በጋራ በመሆን (ዊጆ) የተሰኘ የቅቤ እቁብ በመግባት ለበዓሉ የሚሆን ቅቤ ማጠራቀም ይጀምራሉ፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ ለአተካናና ለሥጋ መብያ ናቀሮ ወይም ዳጣን እንዲሁም የሚጠጣ ቦርዴ፣ ቃሪቦ፣ ጠጅ፣ ብርዝ የማዘጋጀት ድርሻ የእናቶች ነው፡፡ ለበዓሉ የቤት ውስጥና የውጭ ግርግዳን በቀለምና በተለያዩ ጌጣጌጦች የማስዋብ ሃላፊነት ደግሞ የልጃገረዶች ነው።

ወጣት ወንዶች ከነሀሴ መግቢያ ጀምሮ አባቶቻቸው የሚያሳዩዋቸውን ግንድ በመቁረጥ ለምግብ ማብስያ እንዲውል ፈልጠው ያዘጋጃሉ። በሀዲያዎች አጠራር ለችቦ የሚሆን እንጨት ወይም ጦምቦራ ከጫካ ለቅመው አስረው እንዲደርቅም ያስቀምጣሉ፡፡ ለበዓሉ ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት የሚያደርገው ጥረት በዓሉ በስኬትና በድምቀት እንዲከበር ጠቀሜታው የጎላ ነው። በዚህም ያሆዴ ከተናጠል ይልቅ ትብብርን የሚያጠናክር ነው ማለት ይቻላል። እሴቱ በትብብር መድመቅ እንደሚቻልም የሚያሳይ ነው። 


 

ይህን ሀሳብ የሚጋሩት አቶ መስፍን የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል በምንም ሁኔታ መነጣጠል የማይቻል ትስስርን  ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ። ሀገራዊ አንድነትና አብሮነትን የሚያጠናክር ዘመናትን የተሻገረና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ባህላዊ እሴት ያለው መሆኑንም ይናገራሉ።

በዓሉ ሊከበር ጥቂት ቀናት ሲቀረው አባውራዎች በቅርጫ ማህበራቸው አማካኝነት ያጠራቀሙትን ገንዘብ በመያዝ የእርድ በሬ ይገዛሉ። በዚህ ወቅት ገንዘብ ማዋጣት ያልቻሉ የቅርጫ አባላት እህል በሚደርስበት ወቅት ለመክፈል ተስማምተው በሬውን በዱቤ እንዲገዙ ይደረጋል፡፡ ይሄም የሚሆነው በያሆዴ በዓል አንዱ ሲበላ ሌላው ተመልካች መሆን ስለሌለበት ነው። እርስ በርስ መጨካከን እንዳይኖርና በዓሉን በአብሮነት ሁሉም ተደስቶ ማክበር እንዲችል ለማድረግ ነው።

ከበዓሉ ዕለት በፊት ያለው የመጨረሻ ገበያም የእብድ ገበያ (መቻዕል ሜራ) የሚል ስያሜ አለው። ይሄ ሥያሜ ያገኘው በዓሉ ሲቃረብ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚፈጠረውን ውጥረት ታሳቢ በማድርግ ነው፡፡ በዚህ የእብድ ገበያ ህብረተሰቡ መገበያየት የሚጀምረው ጠዋት ማለዳ  ጀምር ሲሆን የግብይት ሂደቱ የሚጠናቀቀው ደግሞ እኩለ ቀን ላይ ነው፡፡

ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለመግዛትና የያሆዴ በዓል ከተከበረ በኋላ ለአንድ ወር ገበያ ስለማይቆም ይህን ታሳቢ ያደረገ ግብይት ለመፈጸም የግብይት ሂደቱ ጥድፊያ የበዛበት ሆኖ ይታያል።


 

ያሆዴ በዓል መከበር የሚጀምረው በአተካን ሂሞ ወይም በአተካና ምሽት ሲሆን ይህም ከበዓሉ አንድ ቀን በፊት ያለው ምሽት ነው። ስያሜውን ያገኘው "አተካና" ከተሰኘና በያሆዴዎች ዘንድ ለክብር እንግዳ እና በዘመን መለወጫ ከሚዘጋጅ ምግብ ነው።

አተካና ከወተት፣ ከአይብ፣ ከቡላ፣ ከቅቤና ከሌሎች የቅመማ ቅመም ውጤቶች የሚዘጋጅ ምግብ ሲሆን በጣም ጣፋጭና የምግበ ፍላጎትን የሚጨምር ምግብ ነው፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ይሄንን የተለየ ምግብ ተሰባስቦ በአብሮነት በመመገብ በደመቀ መልኩ በዓሉን ማክበር ይጀምራል፡፡

የአካባቢው አባቶች በወጣቶች የተዘጋጀ የማቀጣጠያ እንጨት (ሳቴ) ይዘው ትልቅ በሚባሉ አባውራ ቤት ደጃፍ ወደ ተዘጋጀው  የችቦ ደመራ (ጦምቦራ) ቦታ ይመጣሉ:: የሀገር ሽማግሌች አዲሱ ዓመት የብርሃን ዓመት እንዲሆን፤ ለሀገርና ለህዝቦቿ ሰላም እንዲጸና፤ አብሮነት እንዲጠናከር፣ ሰላምና ፍቅር እንዲነግስ ፈጣሪያቸውን ከተማጸኑ በኋላ ችቦውን በእሳት ይለኩሳሉ፡፡


 

ችቦው ከተለኮሰ በኋላ የአካባቢው ወጣቶች ተሰባስበው ያሆዴ …ያሆዴ! …ያሆዴ! በማለት እየጨፈሩ ያነጋሉ ይጨፍራሉ::  በሀድያዎች ዘንድ "ያሆ" ማለት የአዲስ ዓመት መግባትን ተከትሎ ማብሰሪያ ጭፈራ ሲሆን "ኤዴ" ማለት ደግሞ አገናኝ ማለት ነው፡፡

በያሆዴ በዓል የእርድ ሥነ ስርዓት ለማከናወን ነዋሪዎች የሚሰበሰቡበት ስፍራ "ነፈራ" የሚል ስያሜ አለው። የተለያዩ ማህራዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን ለመከወን እንዲመች ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ሰፋ ያለ ቦታ ሰሆን በተለያዩ የጥላ ዛፎች የተዋበና ለዚሁ ተግባር የተዘጋጀም ነው።

በእለቱ ለእርድ የተዘጋጀው ሠንጋ ከቀረበ በኋላ የባህል ሽማግሌዎች የበሬውን ሻኛ በሰርዶ ሳር ለጋ ቅቤ ይቀባሉ፤ ወተትም ያፋሱበታል፡፡ ይህ ባህላዊ ሥነ ስርዓት ጋቢማ የሚባል ሲሆን (የመልካም ምኞት) መግለጫ ስነ ስርዓትም ነው፡፡

ይህም ሥነስርአት በሚከናወንበት ወቅትም "ክፉ ቀን አይምጣ፣ ርሃብ ሰቀቀን ይጥፋ፣ ጥጋብ ይስፈን፣ በአካባቢው በሀገሩ ጥጃ ይቦርቅ፣ ልጅ ይፈንጭበት፣ አገር ሰላም፣ ገበያ ጥጋብ ይሁን፣ ሰማይና ምድሩ ይታረቁን " እያሉ በአባቶች ምርቃት ከተካሄደ በኋላ የእርድ ስነ ስርዓት ይከናወናል፡፡

የእርድ ሥነ ስርዓቱ የተከናወነበት ቤት እማወራ አስቀድመው ባደረጉት ዝግጅት መሰረት ቅቤ፤ (ቦርዴ፣ ቃሪቦ፣ ጠጅ፣ ብርዝ) እንዲሁም ከታረደው የበሬ ሥጋ አርዚ ማራ (ቅምሻ) ይወሰድና ክትፎ ከተዘጋጀ በኋላ በጋራ እየበሉ እየተጫወቱ ይውላሉ፡፡

በዚህም በቅርጫ ሥጋው ላይ ከሚሳተፉት የቤተሰብ አባላት ውጪ በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችም ጭምር አብረው በመብላት በመጠጣት በዓሉን በአንድነት ያሳልፋሉ፡፡ ቀሪውን የቅርጫ ሥጋም አባላቱ ተከፋፍለው ወደ እየቤታቸው ይወስዱታል፡፡  

በዓሉ አብሮ የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመጠያየቅ፣ ችግርንና ግጭትን በጋራ ተወያይቶ የመፍታት፣ መፈቃቀርና መተሳሰብን የሚፈጥር፣ አቅመ ደካሞችና የተቸገሩ የሚረዱበት የአብሮነት መገለጫ በመሆኑ በተለየ መልኩ ይከበራል፡

ከእርድ ሥርዓቱ በኋላ በማግስቱ ልጆች አደይ አበባ (ዘራሮ) ይዘው ወደ ወላጆቻቸው እየጨፈሩ ይመጣሉ። የመስቀል አበባ እንደሚኖር ኑሩ ይባላሉ። ከስጋውም፣ ከቦርዴውም፣ ከአተካናውም እንዲመገቡ ያደረጋል። ይህ ስነ ስርዓትም ሚክራ ይባላል።

በያሆዴ የዘመን መለወጫ በዓል ትዳር የያዙ ሴት ልጆችም ከባሎቻቸው ጋር ሆነው ወደ ወላጆቻቸው ምግብ ሰርተው፣ የሹልዳ ሥጋና አደይ አበባ ጭምር ይዘው ይሄዳሉ። በዓሉ ያላገቡ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ለአዲስ ህይወት ጅማሬ የሚያበስሩበት በመሆኑን የተለየ ድባብ አለው፡፡

የያሆዴ በዓል ካሉት እሴቶች አንዱ የህብረተሰቡን የአካባቢ ልማት ተሳትፎ ማበረታታት ተጠቃሽ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን ዕሴቱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለማህበረሰብ ጥቅም እንዲውሉ ጭምር አቅም እየሆነ መምጣቱን ነው የሚናገሩት።ይህ የአብሮነት ማስተሳሰሪያና የማህበራዊ መስተጋብር መጋመጃ የሆነው በዓል እሴቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል መስራት ይገባል።

እሳቸው እንዳሉት በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ለማስቻል እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም መምሪያው ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ዕሴቱን የመሰነድና ምርምሮች ማካሄድን ጨምሮ እያከናወናቸው ያሉ የተለያዩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም