የአፍሪካ ህብረት የገጠር ሴቶችን ኑሮ ለመቀየር የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት የገጠር ሴቶችን ኑሮ ለመቀየር የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት የገጠር ሴቶችን ኑሮ ለመቀየር እና በአህጉሪቷ የማካካሻ ፍትህን ለማረጋገጥ በበለጠ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ የገጠር ሴቶች ቀን በአፍሪካ ደረጃ ዛሬ በአህጉሪቷ መዲና አዲስ አበባ ዛሬ ይከበራል።
“የገጠር ሴቶችን በማካካሻ ፍትህ አማካኝነት ማብቃት፤ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ስርዓተ ምግብን ማረጋገጥ” የቀኑ መሪ ሀሳብ ነው።
በቀኑ አከባበር ላይ የአፍሪካ ህብረት አመራሮች፣ የመንግስታት ተወካዮች፣ የገጠር ሴቶች አመራሮች እና ተወካዮች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ የዳያስፖራ ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች እና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ይሳተፋሉ።
የቀኑ አከባበር አካል የሆነ የቴክኒክ ውይይት ትናንት የተካሄደ ሲሆን የአፍሪካ የገጠር ሴቶች መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና ባለሙያዎች ሴቶችን ለማብቃት በየሀገራቱ እየተተገበሩ ያሉ ኢኒሼቲቮችን አስመልክቶ የእውቀት እና የተሞክሮ ልውውጥ አድርገዋል።
ዛሬ በሚኖረው ዋናው የቀኑ አከባበር የከፍተኛ ባለስልጣናት ቁልፍ ንግግሮች፣ የፓናል ውይይቶች፣ የገጠር ሴቶች ኢኒሼቲቭ የተሞክሮ ማጋራት መርሃ ግብሮች እና አውደ ርዕዮች ይካሄዳሉ።
ሁነቶቹ የገጠር ሴቶች በትምህርት፣ ቴክኖሎጂ እና በግብርና መካናይዜሽን አማካኝነት የሚበቁባቸው የኢኖቬሽን አማራጮች የሚቀርቡባቸው ናቸው።
ዓለም አቀፍ የገጠር ሴቶች ቀን ከአፍሪካ ህብረት የ2025 መሪ ሀሳብ ከሆነው “የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ለዘርዓ አፍሪካውያን” የተሳሳረ መሆኑ ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የማሻሻሻ ፍትህ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አካሄድ መሆኑን አመልክቷል።
የቀኑን አከባበር ተከትሎ የጋራ አቋም መግለጫ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የጋራ መግለጫው አፍሪካ ስርዓተ ጾታን ባማከለ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ስራ፣ የገጠር ሴቶችን በማብቃት እንዲሁም ማካካሻ ፍትህ እኩልነት የተረጋገጠበትና የማይበገር ስርዓተ ምግብ ለመገንባት ያላትን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያመላክት እንደሆነ ተገልጿል።
የዓለም የገጠር ሴቶች ቀን የአፍሪካ ህብረት የስርዓተ ጾታ እኩልነት ለማረጋገጥ እና በማካካኛ ፍትህ አማካኝነት በገጠሪቷ የአፍሪካ አካባቢዎች የሚገኙ ሴቶችን ለማብቃት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጿል።
ህብረቱ ቀኑን ሲያከብር የበለጸገች፣ ሁሉን አቃፊ እና ዘላቂነትን ያረጋገጠች አህጉር ለመገንባት ባለው መሻት ውስጥ ሴቶች እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ወደኋላ እንዳይቀሩ ዳግም ቃል ኪዳኑን የሚያድስበት እንደሆነ አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ በ2007 ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ባፀደቀው የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 62/136 አማካኝነት ዓለም አቀፍ የገጠር ሴቶች ቀን እ.አ.አ ኦክቶበር 15 እየተከበረ ይገኛል።
ቀኑ በገጠር የሚገኙ ሴቶች ለግብርና፣ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ዘላቂ ልማት ያላቸው ወሳኝ አበርክቶዎች የሚዘከርበት ነው።