"የኦሞ ቻይልድ የወደፊት መሪዎች አካዳሚ"- የዕልፍ ሕጻናት አድኑ ላሌ ላቡኮ አዲስ ፍኖት

 

ሚንጊ የታዳጊዎችን ተስፋና ሕልም ብቻ ሳይሆን ሕልውና የነጠቀ ጎጂ ባህላዊ ልማዳዊ ድርጊት ነው።

በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን እንደ ካራ፣ ሀመርና ቤና ህዝቦች ዘንድ የሚዘወተረው ሚንጊ፤ በአካባቢው ልማድ በታችኛው ድድ ጥርስ የሚያበቅሉ እንስሳት ቅዱስ፣ በላይኛው ድድ ጥርስ የሚያበቅሉ እንስሳት ደግሞ ርኩስ የሚል ስያሜ ይሰጣል።

የላይኛው የወተት ጥርሳቸው ቀድሞ የሚበቅል ሕጻናት እንደ እርኩሳን እንስሳት ከመጥፎ መንፈስ ጋር ተቆጥሮ ለማህበረሰቡ የማይበጅ፣ አድጎም ለቤተሰቡ ጠንቅ ተቆጥሮ የመገደል ዕጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል።

በተመሳሳይ በማህበረሰቡ አባል ሴት ከትዳር በፊት ልጅ ከወለደች የተወለደው ሕጻን በ'ሚንጊ'ነት ይፈረጃል።

በ'ሚንጊ'ነት የተፈረጁ ሕጻናት ደግሞ መርገምት፣ ቁጣ፣ ርሀብ በሽታ… መንስዔ እንደሚሆኑ ታምኖ ከጥልቅ ወንዝ መጣል፣ ወደ ገደል መወርወር አልያም በጫካ ውስጥ የመጣል መጥፎ ዕጣ ይጠብቃቸዋል።

ቤተሰባቸውን በዚህ ጎጂ ባህላዊ ድርጊት ያጡት አቶ ላሌ ላቡኮ 'ሚንጊ'ን ከመሰረቱ ለመንቀል 'የኦሞ ቻይልድ' መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋም ውጤታማ ስራዎች አከናውነዋል።

አሁን ደግሞ የእስካሁን ጥረቶችን ተቋማዊ መልክ በመስጠት 'ሚንጊ'ን በዘላቂነት ማስቀረት የሚያስችል ተቋም አስመርቀዋል።

ይህም በደቡብ ኦሞ ዞን ካራ-ዱስ ቀበሌ በዛሬው ዕለት የተመረቀው "የኦሞ ቻይልድ የወደፊት መሪዎች አካዳሚ'' ነው።

አካዳሚውን በምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።

ዕልፍ ህፃናትን ሕይወት የቀጠፈና ወላጆችን የወላድ መካን ያደረገውን የሚንጊ "ልብ ሰባሪ" ድርጊት ለማስቀረት እንደ ላሌ ላቡኮ ባሉ ቅን ልቦች ብርቱ ተጋድሎ መልከ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ቢሮ ኅላፊው ገልጸዋል።

ያም ሆኑ ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በዘላቂነት ለማጥፋት የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅ ይናገራሉ።

በዕለቱ የተመረቀው አካዳሚም የክልሉ መንግስት በአርብቶ አደሩ አካባቢ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ከባህል ተፅዕኖ ተላቀው መማር እንዲችሉ የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል።

በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ይገልጻሉ።

ሚንጊን ለማስቀረት ከማህበረሰቡ የባህል መሪዎች ጋር በመቀናጀት በተከናወኑ ስራዎች የአስተሳሰብ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ያነሳሉ።

እናም ወትሮ በ'ሚንጊ'ነት የሚፈረጁ ሕጻናት ዛሬ ላይ "የአብራካችን ክፋይ፤ የኛ ልጆች" ተብለው በወላጆች ዕቅፍ ማደግ መጀመራቸውን ይገልጻሉ።

የኦሞ ቻይለድ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ላሌ ላቡኮ፤ "ይህን መሰል ጎጂ ልማድ ድርጊት ማስወገድ በቀላሉ የሚታሰብ ሳይሆን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የሚጠይቅ ዋጋ መክፈል ይጠይቃል" ይላሉ።

ያም ሆኖ ራሳቸውን ለመስዕዋትነት ዝግጁ በማድረግ ድርጊቱ እንዲቀር ማድረግ ስለመቻላቸው ያነሳሉ።

በእርሳቸው ድርጅት ብቻ ላለፉት 15 ዓመታት ከ60 በላይ በ'ሚንጊ'ነት የተፈረጁ ሕጻናትን ሕይወት እና ሕልም በመታደግ ለሀገር ኩራት እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።

"ትምህርት ባይኖር በልበ ሙሉነት ማውራት አልችልም ነበር" የሚሉት አቶ ላሌ፤ "የኦሞ ቻይልድ የወደፊት መሪዎች አካዳሚ'' ባለብሩህ አዕምሮ ሀገር ተረካቢ ሕፃናት የሚፈልቁበት ማዕከል እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም