ሠራዊቱ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምን የማፅናት ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል - ሜጀር ጄኔራል አድማሱ አለሙ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምን የማፅናት ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል - ሜጀር ጄኔራል አድማሱ አለሙ

ወልዲያ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦መከላከያ ሠራዊት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምን የማፅናቱን ተግባር አጠናክሮ መቀጠሉን በመከላከያ ሠራዊት የ11ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አድማሱ አለሙ ገለጹ።
"ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ በወልዲያ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር፣ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች እና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በመከላከያ የ11ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል አድማሱ አለሙ እንዳመለከቱት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጽንፈኛውን ቡድን ከአካባቢው የማፅዳት ተግባር በውጤማነት ቀጥሏል።
ሠራዊቱ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምን የማፅናት ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ ለዚህ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አመልክተዋል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው በበኩላቸው፤ ባዕዳን በራሳችን ወገኖች አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የሚያደርጉት ሙከራ አይሳካም ሲሉ ገልጸዋል።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ፤ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ተላላኪ ባንዳዎች በመቀናጀት የአካባቢውን ሠላም ለማደፍረስ እያደረጉት ያለውን ጥረት በጀግናው መከላከያና በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ እየመከነ ነው ብለዋል።
ሰላምን አጽንቶ በማስቀጠል እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ምሁራንና ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲው መምህራን የአካባቢውን ችግር ለመፍታት በእውቀትና በምርምር የታገዘ የመፍትሄ ሀሳብ ማፍለቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።