በዞኑ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል የጸጥታ ሃይሉና የህዝቡ ጠንካራ ትብብር ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል የጸጥታ ሃይሉና የህዝቡ ጠንካራ ትብብር ውጤት እያመጣ ነው

ባሕህር ዳር፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፡-በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል የጸጥታ ሃይሉና የህዝቡ ጠንካራ ትብብር ውጤት ማምጣቱን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ።
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን የባዳን ተልዕኮ በመቀበል የባንዳነት ተግባሩን ለመፈጸም ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የባንዳነት ተልዕኮውን በጸጥታ ሃይሉ እና በክልሉ ህዝብ ጠንካራ ትብብር ከማክሸፍ ባለፈ በጽንፈኛው ላይ ጠንካራ የህግ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።
በክልሉ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ኢዜአ የዞኑን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ጌታቸው ቢሻውን አነጋግሯል።
ኃላፊው በማብራሪያቸው ለሰላምና መረጋጋት ሲባል በመንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በመደረጉ ይህንኑ ጥሪ ተቀብለው የመጡ ታጣቂዎች እንዳሉ አንስተዋል።
ከዚህ የሰላም ጥሪ በማፈንገጥ የጥፋት ተልዕኮ ለመፈፀም በሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን ላይ ግን በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ እርምጃ እና በህዝቡ ትብብር በአካባቢው ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።
የጽንፈኛ ቡድኑ ዓላማ ከባዳዎች የተቀበለውን የባንዳነት ተልዕኮ ለመፈፀም ቢሆንም መንግስት እየወሰደ ባለው ጠንካራ ህግ የማስከበር እርምጃ ዕቅዱ ከሽፎ ተበትኗል ብለዋል።
የተለያዩ ህዝባዊ መድረኮችን በመፍጠር ለህብረተሰቡ የጽንፈኛውን የጥፋት ዓላማ በአግባቡ በማስገንዘብ የሰላሙ ዘብ ሆኖ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም በዞኑ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ የልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ሥራዎች በተሳካ መልኩ መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የሕብረተሰቡን ዘላቂ ሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኃላፊው አረጋግጠዋል።