የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት አንገብጋቢው ጉዳይ - ኢዜአ አማርኛ
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት አንገብጋቢው ጉዳይ

የባህር በር ጉዳይ በሀገራት ዘንድ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ግዙፍ ኢኮኖሚና ሰፊ ህዝብ ላላቸው ሀገራት ሕልውና ጉዳይ ሆኗል። በቱርክሜኒስታን አዋዛ ከተማ ሶስተኛው ባህር በር አልባ ታዳጊ ሀገራት ጉባዔ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም በጉባኤው መክፈቻ ላይ ቁልፍ መልዕክት አስተላለፈዋል። ዋና ፀሐፊው ባህር በር የሌላቸው ሀገራት በተለይም መልኩ እየተለዋወጠ ባለው ዓለም፤ በአየር ንብረት ለውጥና መሰል ተጽዕኖዎች ሳቢያ መልከ ብዙ ፈተና እንደተደቀነባቸው ገልጸዋል። በተለይ ለአንዳንዶቹ ህልውናቸውን እየተፈታተነ ስለመሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዋና ጸሐፊው ንግግርም ፦
ዛሬ ከዚህ የተሰባሰብነው ለማንክደው አንድ ዕውነት ነው። መልክዓ ምድር መዳረሻን መወሰን የለበትም። ነገር ግን በአፍሪካ፣ በኤዥያ፣ በላቲን አሜሪካና በአፍውሮፓ 32 ሀገራት ባህር በር ስለሌላቸው የማደግ ዕድላቸው ተገድቧል፤ ኢ-ፍትሃዊነትንም አስፍቷል።
ሀገራችሁ አያሌ ተግዳሮቶች ተጋርጦባቸዋል። ዕድገታቸው እንዲወሰን፣ በከፍተኛ የወጪ ንግድ ትራንስፖርት እንዲበዘበዙና በዓለም ገበያ ተደራሽ እንዳይሆኑ ፈተና ገጥሟቸዋል።
በርካቶች በጥሬ ዕቃ ኤክስፖርት እንዲወሰኑ፣ ለተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲጋለጡ ብሎም በጠባብ ኢኮኖሚያዊ መሰረት እንዲታጠሩ አድርጓቸዋል።
በሌላ በኩል የዕዳ ጫና ለመልከ ብዙና ዘላቂነት ላለው ችግር ዳረጓቸዋል። አንድ ሶስተኛው የዓለማችን ባህር በር አለባ ሀገራትም ለደህንነት እንዲጋለጡና የግጭት አዙሪት ችግር እንዲገጥማቸው ተገደዋል። ምንም እንኳን 7 በመቶው የዓላማችን ህዝብ ድርሻ ቢይዙም በዓለም ኢኮኖሚ አንድ በመቶ ብቻ ድርሻ ይዘዋል። ይህም ምንጊዜም ኢ-ፍትሃዊነትና መገለል ሁነኛ ማሳያ ነው። ይህ የኢ-ፍትሃዊነት መልክ ዘላለማዊ መሆን የለበትም።
ባህር በር የሌላቸው ሀገራት በዓለም የፋይናንስና የንግድ መዋቅር ውስጥ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ናቸው። በበይነ-ዓለም ትስስር በገሀድ በሚታይበት የዛሬው የዓለም መልክ ስርዓታዊ መድሎና መገለል በይፋ የደረሰባቸው ሀገራት ናቸው። ይህም በብዙ ምክንያቶችም የቅኝ ግዛት አሻራ ምልክት ነው።
በቅርብ ጊዜ ትውስታዎች እንኳን ከኮቪድ 19 እስከ አየር ንብረት ለውጥ ቀውሶች፣ ከአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እስከ ግጭት እንዲሁም በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ሳቢያ ባህር በር የሌላቸው ሀገራት ዘላቂ የልማት ግቦችን ዕውን ለማድረግ ተቸግረዋል።
ይህ ጉባኤ ችግሮችን ከማንሳት ባሻግር መፍትሄዎች ላይ ማተኮር አለበት። የቀጣይ ዘመን የእድገት መሻት ጉዞን መቀየስ ብሎም ባህር በር አልባ ታዳጊ ሀገራትን የማልማት ዕድሎች በጋራ መግለጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምክር ይገባል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በዚህ ረገድ ከሀገራቱ ጎን የቆመ ነው።
በቀጣይ አስርት ዓመታት በትብብር መሰራት ካለባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መዋቅራዊ ሽግግርን ማሳለጥ እና ኢኮኖሚያዊ ስብጥርን ማብዛት ላይ መተኮር ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ ሀገራት በሰው ሃይል እና በተፈጥሮ ሀብት የታደሉ ቢሆንም በፋይናንስ እጥረትና በገበያ እጦት ይህን አቅም ተጠቅመው መልማት አልቻሉም።
ወሳኝ የሆኑ እሴት ጨማሪ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት፣ ሀገር ውስጥ ፈጠራዎችን ማጎልበት እንዲሁም ለቀጣናው ለትውልድ ትሩፋት የሚያቋድስ አካታች ልማትን ዕውን ማድረግ ይሻል።
የሀገራቱን የገበያና የመልክዓ ምድር ተግዳሮቶችን ለማቅለል አንዱ መፍትሄ የዲጂታላይዜሸን ሽግግር ነው። በዲጂታል ምህዳር ተደራሽነት ለማቅለልም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ስራዎች መጠንከር አለባቸው። የግል ዘርፉን ማጠናከርም ኢ-ፍትሃዊነትና ተደራሸነትን ችግርን ለማቅለል ያግዛል።
ሀገራቱ በቋንቋ፣ በባህልና በጥበብ በጥልቅ የተቆራኙ ናቸው። በሀገራቱ መካከል ያለው የተቆራረጠ ሎጂስቲክስ፣ ያልተሳለጠ የድንበር ግብይት፣ የተሟላ መሰረተ ልማት አለመኖር በዓለም ገበያ ተወዳደሪና ተደራሽ ለመሆን አልቻሉም። በመሆኑም ድንበር ዘለል የሆኑ ትስስሮችን ማሳለጥ በተለይም ሀገራትን የሚያስተሳሰሩ ኮሪደሮችን መገንባት፣ የጭነት ሎጂስቲክስን ማሳለጥ፣ የሃይል እና የአየር ትራንስፖርት ትስስርን መጨመር ያስፈልጋል።
ይህን መንገድ በመከተል በቀጣናውና በዓለም ገበያ መግባት ብሎም ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ወደ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ማቅረብ መሸጋገር ይቻላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ ግብይት መልክን መለወጥ፣ የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተቃኘ አካሄድ መከተል ይገባል።
ዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን የፋይናንስ ተቋማትም የበይነ ሀገራት የድንበር ላይ ትስስርና የጋራ ልማት ላይ ተገቢውን የኢንቨስትመነት ልማት ፋይናንስ ማቅረብ ይገባቸዋል። ባህር በር የሌላቸው ሀገራት በቀጣናው ደረጃ ከተሰባሰቡ ልማትን ዕውን ማድረግ ያስችላልና።
ባህር በር አልባ ሀገራት ምንም እንኳን ከዓለማችን ሀገራት የበካይ ጋዝ ልቀታቸው ለከ3 በመቶ ያነሱ ቢሆነም የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ገፈት ቀማሾች ግን እንርሱ ናቸው።
ከሰሃራ በርሃ መስፋፋት እስከ በረዶ የሚቀልጥባቸው ተራራማ ሀገራት፣ የኤስያ ሀገራት አስቸጋሪ የአየር ጸባይ ለውጥ፣ በከባድ ዝናብና አውሎንፋስ የሚመቱ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ለዚህ ማሳያ ናቸው። የአየር ንብረት ለውጥ ባህር በር አልባ ሀገራትን እየበላቸው ነው።
የአየር ንብረት ለውጥና ባህር በር አልባነት ተዳምሮ ዕድገታቸውን እንዲወሰን ለአንዳንዶቹም በህልውናቸው ላይ አደጋ ደቅኗል። በተባበሰው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ሳቢያ በአንድ አዳር በሚደርስ የመሰረተ ልማት ውድመት የሀገራት ዓለም አቀፍ ንግድ ተሳትፎ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። በመሆኑም ቃል የተገቡ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋሚያ ፋየናንስ መተግበር፣ ተዕጽኖ የሚቋቋም መሰረተ ልማት መዘርጋት ይሻል” በማለት ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
በአረንጓዴ ልማት፣ በፋይናንስ ማሰባሰብ፣ በብድር አቅርቦት እና ወለድ አያያዝና ትግበራ ጉዳይም ልብ መባል ያለበትን ጉዳይ ጠቅሰዋል። ባህር በር አልባ ሀገራት በጋራ ነጋቸውን ለማሳመርና ፈተናዎቻቸውን ለመሻገር በትብብር እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ጥያቄዋን በይፋ ከገለጸች ውላ አድራለች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።