የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈፀም አቅም በማጎልበት የህዝቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈፀም አቅም በማጎልበት የህዝቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈፀም አቅም በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ከክልሉ አመራር አካዳሚና ከብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ለክልሉ አመራሮች ያዘጋጀው ስልጠና በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ነው።
"ብቁ አመራር ለላቀ ውጤት" በሚል መሪ ሀሳብ በሚሰጠው የአመራር ስልጠና ላይ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ በየጊዜው የሚሰጡ ስልጠናዎች የአመራሩን አቅም በማሳደግ ሁለንተናዊ የልማት ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ስልጠናው የአመራሩን የመፈፀምና የማስፈጸም አቅም በማሳደግ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እያገዙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ስልጠናዎቹ ከነጠላ ትርክት ይልቅ አሰባሳቢና ገዥ ትርክትን በአመራሩ ላይ በማስረፅ የጋራ ሀገራዊ እሴቶችን ለማጠናከርም አቅም ስለሚፈጥሩ ይጠናከራሉ ብለዋል።
በየደረጃው ያለው አመራርም ከስልጠናው የሚያገኘውን እውቀት በአግባቡ በመተግበር በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ተግቶ እንዲሰራም አሳስበዋል።
የክልሉ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብልሀቱ በበኩላቸው እንደገለጹት አካዳሚው ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚተጉ አመራሮችን እያፈራ ይገኛል፡፡
አካዳሚው ሀገራዊና ክልላዊ ተልዕኮዎችን በብቃት መፈፀም የሚችሉ አመራሮችን ለማፍራት የተለያዩ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።
ስልጠናው በክልሉ ለማከናወን የተያዙ የልማት እቅዶችን በመፈጸም የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማጠናከር አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስልጠናውን እየሰጡ ያሉት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ሲሆኑ በስልጠናው የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡