ከአረብ ሀገር የአመታት እንግልት በኋላ በሀገሩ ህልሙን እውን ያደረገው ወጣት... - ኢዜአ አማርኛ
ከአረብ ሀገር የአመታት እንግልት በኋላ በሀገሩ ህልሙን እውን ያደረገው ወጣት...

ሐረር ፤መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፦በሐረር ከተማ ተወልዶ ያደገው ነስረዲን አህመድ፤ በውጭ ሀገር ሰርቶ መለወጥን በማሰብ ከአመታት በፊት ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ እንቅስቃሴ ጀመረ።
የመጓዝ እቅዱም ተሳካለትና በዱባይ ለስምንት ዓመታት በስራ ላይ ማሳለፉን ያስታውሳል፤ በበረሃው ምድር ሌት ተቀን በስራ እየደከመ ህይወቱን ሊለውጥለት የሚችል ገንዘብ ለመያዝ ቢጥርም ባሰበው ልክ ሊሳካለት አልቻለም።
በመሆኑም ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ በመመለስ ሰርቶ የመለወጥ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ሳይውል ሳያድር ወደ ስራ ገባ።
ከበረሃው ንዳድ ወጥቶ በሀገሩ ሰርቶና አልምቶ መለወጥን የሰነቀው ነስረዲን በሀረር የንብ ማነብ ስራን ከጀመረ ሶስት ዓመታት እንደሆነው ያስታውሳል።
በምንሰራበት የስራ መስክ ሁሉ በትጋት ሌት ከቀን መስራት ከቻልን የማናሳካው ነገር አይኖርም የሚለው ወጣቱ አሁን በሀገሩና በወንዙ በስኬት መንገድ ላይ መሆኑን ይናገራል።
የነስረዲን የንብ ማነብ ስራ የተጀመረው በጥቂት ቀፎዎች የነበረ ቢሆንም በስድስት ወራት ውስጥ ግን 50 ቀፎዎች ማድረስ መቻሉን ያስታውሳል።
በሀገሬ ህልሜ እውን እየሆነ ነው የሚለው ወጣቱ የንብ ማነብ ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል አሁን ላይ የንብ ቀፎዎቹን 300 ሲያደርስ ለ30 የአካባቢው ወጣቶችም የስራ እድል ፈጥሯል።
በአረብ ሀገር የቆየባቸውን ዓመታት በቁጭት የሚያስታውሰው ነስረዲን መልፋትና መድከም ከተቻለ በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል እኔ ጥሩ ማሳያ ነኝ ይላል።
ከአረብ ሀገር የአመታት እንግልት በኋላ ወደ ሀገሬ ተመልሼ የስኬት መንገድን ጀምሬያለሁ በቀጣይም ጠንክሬ እሰራለሁ ብሏል።
በቀጣይ ከንብ ማነብም ባለፈ የማር ማቀነባበርያ አነስተኛ ኢንዱስትሪ የማቋቋም ትልም እንዳለው ተናግሮ ለዚህም እንደሚተጋ አረጋግጧል።
በዚሁ የልማት ፕሮጀክት ላይ የስራ እድል የተፈጠረለት ወጣት ሸዊብ መሀመድ፤ ከዚህ ቀደም ያለምንም ስራ ተቀምጦ መሽቶ ይነጋ እንደነበር አስታውሶ አሁን እያገኘ ባለው ገቢ ከራሱ አልፎ ቤተሰብ እየረዳ መሆኑን ተናግሯል።
ወጣት በድሪ ሙሳም፤ በነስረዲን ጥረት እርሱን ጨምሮ ብዙ ወጣቶች ስራ የተፈጠረላቸው በመሆኑ ጥሩ ገቢ እያገኙ መሆኑን አንስቶ በቀጣይ እርሱም የራሱን ተመሳሳይ ስራ ለመጀመር ማቀዱን ገልጿል።
በሐረሪ ክልል ግብርና ልማት ቢሮ የንብ እርባታ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኢብሳ ዩስፍ፤ የነስረዲን ጥረትና የአጭር ጊዜ ስኬት ለሌሎች ወጣቶችም ጥሩ ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ የማር ምርታማነትን ለማጎልበት በከተማና በገጠር ወረዳዎች ላይ የንብ መንደር በመመስረት ዘርፉን የማጎልበት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።