በቀጣናው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል የተጀመሩ የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣናው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል የተጀመሩ የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢጋድ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) በቀጣናው የሚታየውን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር የጀመራቸውን የተቀናጀ ምላሽ የመስጠት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የኢጋድ ሶስተኛው የሰራተኛ፣ ስራ እና የሰራተኛ ፍልሰት የሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ ተጀምሯል።
“በኢጋድ ቀጣና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሰራተኛ ፍልሰት እና የሰዎች ዝውውር ህጋዊ ማዕቀፍን ማሻሻል” የስብሰባው መሪ ቃል ነው።
በስብሰባው ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት የሰራተኛ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኤልኦ)፣ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(አይኦኤም)፣ የአውሮፓ ህብረትና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።
በኢጋድ ቀጣና የሰራተኛ፣ ስራ እና የሰራተኛ ፍልሰት ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በቀይ ባህር መስመር ያለውን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ይካሄዳል።
በስብሰባው ላይ ከኢጋድ ቀጣና ውጪ የሚገኙ ዜጎች አባል ሀገራትን በነጠላ የመግቢያ ቪዛ መጎብኘት የሚያስችላቸውን የቪዛ ኢኒሼቲቭ ይፋ ይደረጋል።
ኢኒሼቲቩ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርና ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ማሳለጥ እንዲሁም ቱሪዝምን የማሳደግ ፋይዳ እንዳለው ኢዜአ ከኢጋድ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአውሮፓ ህብረት የፋይናንስ ድጋፍ የሚተገበረው ነጻ የሰዎችና የቁም እንስሳት እንቅስቃሴ የህግ ማዕቀፍ ሁለተኛ ምዕራፍ ይፋ ይሆናል።
ማዕቀፉ ህጋዊ የፍልሰት መንገዶች ለማጠናከር እና ቀጣናዊ ትስስርን የማሳካት ግብ ያለው መሆኑንም አመልክቷል።
ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለትን መበጣጠስ፣ በፍልሰት በሌላ ሀገር የሚገኙ ዜጎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ላይ ምክክር ያደርጋሉ።
በውይይቱ ማብቂያ ሀገራት የጋራ መግለጫ እንደሚያወጡ የሚጠበቅ ሲሆን ደህንነቱ የተጠበቀ መደበኛ ፍልሰት፣ ጠንካራ የሰራተኛ አስተዳደር ስርዓት መፍጠርና ለሰዎች ዝውውር የተቀናጀ ቀጣናዊ ምላሽ መስጠት ላይ የጋራ ቁርጠኝነታቸውን እንደሚገልጹ ተጠቁሟል።
ኢጋድ በቀጣናው የሚታየውን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር የጀመራቸውን የጋራ ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክቷል።
ዜጎች ህጋዊ አማራጮችን እንዲከተሉና የኢኮኖሚ ፈተናን ጨምሮ ለሌሎች ገፊ ምክንያቶች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጿል።
ስብሰባው ጥቅምት 10 እና 11 በባለሙያዎች፣ ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ደረጃ ይካሄዳል።