ቀጥታ፡

ጉባዔው በጤናው ዘርፍ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ማስፋት የሚያስችሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ነው - ዶክተር ደረጄ ዱጉማ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ 27ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ በዘርፉ የተጀመረውን የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ማስፋት የሚያስችሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለፁ።

ጉባዔውን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የክልል ጤና ቢሮ እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የቡድን ውይይት እያደረጉ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በሰጡት መግለጫ ፤ ጉባዔው "ዘላቂ ኢንቨስትመንት እና ኢኖቬሽን ለጠንካራ የጤና ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

ባለፉት ዓመታት የታዩ ውጤታማ ተግባራትን ማስፋትና ማስቀጠል እንዲሁም ችግሮችን ማቃለል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል። 

የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የልምድ ልውውጥና ውይይት መካሄዱንም ጠቅሰዋል።                       

ዶክተር ደረጄ አክለውም፣ በጉባዔው ለዜጎች ጤና መሻሻል የሚያገለግሉ ኢንቨስትመንቶችን ፈሰስ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለዋል።

የመንግሥትና የግል አጋርነትን ማጠናከር የጉባዔው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አመልክተው፤ የግሉን ዘርፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ ያለውን የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻል የሚያስችሉ ውሳኔዎች በጉባዔው እንደሚተላለፉም ገልጸዋል።

የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል፣ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን ለማስፋትና የጤና ሥርዓቱን በዘላቂ ሀገራዊ ኢንቨስትመንትና ኢኖቬሽን መደገፍ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት ተናግረዋል።

 

 

                                        

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም