ቀጥታ፡

ምርታማነትን ለማሳደግ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና የአፈርና ውሃ ጥበቃን ማጠናከር ይገባል

አዳማ፤ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፡-ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና የአፈርና ውሃ ጥበቃን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የንቅናቄ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ዛሬ ተጀምሯል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ገመቹ በወቅቱ እንዳመለከቱት፥ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ድርቅና የጎርፍ አደጋዎችን ለመመከት አግዘዋል።


 

በተለይም በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኖችን የመንከባከቡ ስራ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋምና የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣የደረቁ ሃይቆች፣ወንዞችና ዥረቶች ተመልሰው ለመስኖና ለተለያዩ ልማቶች እንዲውሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በበጋ ወቅት የተገነቡ የተፋሰስ ልማቶችን በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ በመሸፈንና በመንከባከብ ውጤት መገኘቱንም አንስተዋል።

ተግባሩንም ለማዝለቅ የችግኝ እንክብካቤ የንቅናቄ ሳምንትን በማወጅ በዛሬው ዕለት የክልሉ ግብርና ሴክተር አመራሮችና ሰራተኞች በምስራቅ ሸዋ ዞን ማስጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በችግኝ እንክብካቤው አረም በማንሳት፣የመኮትኮትና ውሃን በማጠጣት ችግኞቹ የበጋውን ወቅት እንዲቋቋሙ መስራት ይገባል ብለዋል።

በንቅናቄው ማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት ከድር መሐመድ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ እንዲያድጉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ እንዳልሆነ ተናግረው፤የተተከሉትን ችግኞች በየጊዜው በመንከባከብ ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ አለብን ብለዋል።

ዘርፌ ማሞ በበኩሏ፥ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በቀዳሚነት የሚጎዱት ሴቶች በመሆናቸው ለመፍትሔው ላለፉት ሰባት ዓመታት በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም