ቀጥታ፡

 በከምቦልቻ ከተማ  በትምህርት ዘመኑ ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ  ይሆናሉ 

ከምቦልቻ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፡ -በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ በተያዘው የትምህርት ዘመን  ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ  እንደሚሆኑ የከተማው አስተዳደር  ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። 

በከተማው አስተዳደር  የ2018 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ዛሬ ተጀምሯል። 


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት  የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በእውቀትና በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው።


 

በከተማው  የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ ግብዓት በማሟላት፣ የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስና በምገባ ፕሮግራም  የመደገፍ  ተግባር ሲከናወን  ቆይቷል። በዚህም  አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የተገኘውን  ውጤት ለማስቀጠል ከተማ አስተዳደሩ ከመደበው በጀት በተጨማሪ ባለሃብቶችን፣ ድርጅቶችና ሌሎችንም አካላት በማስተባበር የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም ዛሬ ተጀምሯል ብለዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግስቱ አበበ በበኩላቸው፤ ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በከተማው የተማሪዎች ምገባ መጀመሩን አስታውሰዋል።


 

በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም በ20 ትምህርት ቤቶች ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ  ሥራው ዛሬ  በይፋ ተጀምሯል ብለዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ ፈለገ ጥበብ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ሐይማኖት ጋረድ ፤ የምገባ ፕሮግራሙ በትምህርት ቤቱ ከተጀመረ ወዲህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት  እንዲከታተሉና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማገዙን ገልጸዋል።


 

በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም ከ700 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ  ላይ  የከተማው አመራሮችና  ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም