በ600 ዓመታት አንድ ጊዜ 7 ቀናት የሚኖሯት ጳጉሜን… - ኢዜአ አማርኛ
በ600 ዓመታት አንድ ጊዜ 7 ቀናት የሚኖሯት ጳጉሜን…

ጳጉሜን በሦስት ዓመታት አምስት፣ በአራት ዓመታት ውስጥ ስድስት እንዲሁም በ600 ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ሰባት ቀናት ይኖሯታል።
👉 ‘ጳጉሜን’ ማለት ምንድን ማለት ነው?
‘ጳጉሜን’ የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል መምጣቱን በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነገረ መለኮትና የሥነ-ልቡና መምህር አባ ጌዴዎን ብርሀነ ይገልጻሉ።
ትርጉሙም “ተውሳክ ወይም ተረፍ” ማለት መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።
(አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭) ላይም “በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን ተጨማሪ ሆና የምትመጣ መሆኗ ተገልጿል።
በዚሁ መሠረት በሦስት ዓመት አምስት፤ በአራት ዓመት (በዘመነ ዮሐንስ) ስድስት እንዲሁም በ600 ዓመታት አንድ ጊዜ ሰባት ቀናት እንደምትሆን ተመላክቷል።
👉 የጳጉሜን መሠረት?
ይህን በተመለከተ መምህር አባ ጌዴዎን ሲያስረዱ፤ በየቀኑ የሚተርፉ ተረፈ ደቂቃዎችና ሰከንዶች ቀናትን እያስገኙ ተጠራቅመው ከዓመቱ በስተመጨረሻ አምስት ዕለታት ይተርፋሉ ይላሉ።
በዚህም ጳጉሜን የተባሉ አምስት ዕለታት እንደሚገኙ ጠቁመው፤ አንድ ዓመት ደግሞ 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልኢት ይሆናል ሲሉ ይገልጻሉ።
15ቱ ኬክሮስ በአራት ዓመት ስድስት ጳጉሜንን ይወልዳል ያሉት መምህሩ፤ ስድስቱ ካልኢት ደግሞ በ600 ዓመት ሰባተኛ ጳጉሜንን ያስገኛሉ በማለት አብራርተዋል።
👉 ከጭማሬ ቀንነት በተለየ ያላት ትርጓሜ ምንድን ነው?
እንደ መምህር አባ ጌዴዎን ገለጻ፤ ‘ጳጉሜን’ ከተጨማሪ ቀናትነት የተሻገረ ለኢትዮጵያውያን የማንነት ዐሻራ የእኩልነት ምልክት ናት።
በዓለም ዘንድ ባለው የበላይነት እና ሌላውን አሳንሶ የማየት ዝንባሌ እንደነዚህ ያሉ የጥበብ መንገዶች የኢትዮጵያውያንን ማንነትና በዓለም ዘንድ የነበራቸውን የቀዳሚነት ቦታም ከሚያሳዩ ምልክቶች መካከል አንዱ በመሆኑ የማንነት መገለጫ ናት ይላሉ።
ምክንያቱም ከማንም ያልተወሰደ የራስ ማንነት መኖሩ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በዓለም ዘንድ የነበራቸውን የመፈላሰፍ፣ የስልጣኔና አካባቢያቸውን በንቃት የመገንዘብ አቅም የሚያሳይ ስለሆነ ብለዋል።
ጳጉሜን ኢትዮጵያን ከቀደምት ስልጡን ሀገራት መካከል ቀዳሚ የስልጣኔ ፋና የፈነጠቀባት ለመሆኗ ማሳያ ስለመሆኗም ይናገራሉ።
የሰው ልጅ አካባቢውን በንቃት መገንዘብ መጀመሩ እና የሰማያዊ አካላትን የማይዋዥቁ ክስተቶች በመከታተል የማይታየውንና የማይሰፈረውን የጊዜ ርዝማኔ በብርሃናት እየሰፈረና እየለካ፤ ዕለታትን፣ ሳምንታትን፣ ወራትን፣ ወቅትን፣ ዓመታትን፣ አዝማናትን እና ሌሎች ዐውዳትን መቀመሩን ጠቅሰዋል።
በዚህም የጊዜ ልኬት ከሥነ-ፈለክ እና ከሐሳበ-ከዋክብት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።
በአጭሩ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ከሚያዩአቸው ተደጋጋሚ ሁነቶች በመነሳት የጊዜ አሃዶችን ወስነዋል፤ ክፍፍሎችንም በይነዋል ብለዋል መምህር አባ ጌዴዎን።
በተለይም ለዕይታቸው ቅርብ የሆኑት የፀሐይ እና የጨረቃ ያለማቋረጥ መውጣት እና መግባት፣ የሚወጡበት እና የሚገቡበትም የጊዜ መጠን በአንጻራዊነት ቋሚ በመሆኑ ለቀን አቆጣጠራቸው ዋነኛ ግብዓቶች እንደሆኗቸው ተናግረዋል።
በሂደትም የዑደታቸውን የጊዜ መጠን በሚገባ ተረድተው፣ የዑደታቸውን ህጸጾች ዐወቁ ይላሉ።
በዚህ ብቻ ሳይገደቡ የሰማይ አሰሳን ከፀሐይ እና ጨረቃ ወደ ሌሎች አፍላካት፣ ወደ ከዋክብትም ጭምር ማስፋታቸውን ነው የሚገልጹት።
በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ የራሳቸው የቀን መቁጠሪያ ቀመር ካላቸው ቀደምት ሀገራት መካከል አንዷ መሆን መቻሏን አስገንዝበዋል።
ለዚህም በዋቢነት ከሚጠቀሱት ጥንታዊ መዛግብቶቿ መካከል መጽሐፈ ሄኖክን እና አቡሻኽርን አንስተዋል።
👉 ከነበረው ወደ ሌላኛው ዓመት መሻገሪያ እንደመሆኗ ሰዎች በዚህ ወቅት ምን አይነት ሥነ-ልቡናዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ ይመከራል?
ጊዜ የለውጥ መስፈሪያ (መለኪያ ወይም መለያ ድንበር) መሆኑን የሚገልጹት መምህር አባ ጌዴዎን፤ ለውጥ ያለጊዜ፣ ጊዜም ያለ ለውጥ አይሆኑም፤ ትርጉምም የለውም ይላሉ። ጊዜ በዚህ ዓለም የማይቋረጥ ሂደት፤ የማይቆም የለውጥ ጥያቄ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
በዚህ የለውጥ ምክንያት የሰው ልጅ የሚኖረው ከተሰጠው ወይም ካለው እየቀነሰ እንጅ እየጨመረ እንዳልሆነም ይጠቅሳሉ።
ስለዚህ ጳጉሜን የማንቂያ ደወል ናት፤ የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ አዲስ ዘመን በለውጥ ምክንያት የተገኘ በመሆኑ ከነበረው የዕለታት ድምር ባሻገር አዲስ የሚል ቅጽል ይዞ መጥቷል ይላሉ።
ስለዚህ ጳጉሜን ምን አዲስ ነገር አለ የሚል የሕይወት ጥያቄ አስከትላ የመጣች በልባችን ምኅዋር የምታቃጭል ናት ብለዋል።
በጳጉሜን ብዙዎች በጽሞና ሆነው ራሳቸውን የሚያዳምጡባት ወደውስጥ በጥልቀት የሚመለከቱባት በመሆኗ ባለፉት ጊዜያት ያልተሳኩትን በቀጣይ ለማሳካት አዳዲስ ሐሳቦችን እና እቅዶችን በማዘጋጀት ለቀጣዩ ምዕራፍ የምታሻግር ናት በማለት ገልጸዋል።