ቀጥታ፡

ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች  

ጎንደር ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ በመሳተፍ  ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጎንደር ከተማና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች አስታወቁ።

ሠላምና ልማት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።    


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል  ቄስ ሞገስ መልኬ እንዳሉት፤ የአካባቢው ሰላም ፀንቶ ልማት እንዲጠናከር በሚደረገው እንቅስቃሴ ወስጥ በንቃት በመሳተፍ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።


 

በመንግስት የተናጠል ጥረት ብቻ ሠላምን ማረጋገጥ ስለማይቻል ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የድርሻዬን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ ያሉት ደግሞ አቶ መኮንን አዱኛ ናቸው።   

በአካባቢያቸው በሠላም ዘብ በመሳተፍ ሠላምን ለማስቀጠልና ህብረተሰቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።     

የሀገር ሽማግሌው አቶ ወልዴ መና በበኩላቸው፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ጎንደር በታሪኳ የማታውቀው የልማት ተቋዳሽ ለመሆን በቅታለች ነው ያሉት።


 

በመሆኑም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሠላሟን ለማጠናከር በሚሰሩ ሥራዎች አበርክቷቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።  

ሠላምና ልማት እንደማይነጣጠሉ በመገንዘብ ህዝቡ ሠላሙን ለማጽናት እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ መንግስት እውቅና ይሰጣል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አላምረው አበራ ናቸው።  


 

በአካባቢው ሰላምን ለማፅናት በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ማህበረሰቡ የጀመረውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።    

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው ህብረተሰቡ የሠላሙ ባለቤት በመሆኑ ጎንደር ከተማ የልማትና የሰላም ተጠቃሚ ሆናለች ብለዋል።   


 

የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ለከተማው ሠላም መረጋገጥ መስዋዕትነት ጭምር መክፈላቸውን ጠቁመው፤ ዛሬም ይህን ማህበራዊ ሃላፊነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።    

የጎንደርን ልማት፣ ሠላምና እድገት የማይሹ ሀይሎች በየጊዜው ለጥፋት እየተዘጋጁ በመሆኑ ህዝቡ ሠላሙን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።   

በመድረኩ በከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አርሶ አደሮች ሴቶችና ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም