በአማራ ክልል ከ260 ሺህ ሄክታር በሚልቅ መሬት ላይ የተቀናጀ የአፈር እና ውሃ እቀባ ሥራ ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ260 ሺህ ሄክታር በሚልቅ መሬት ላይ የተቀናጀ የአፈር እና ውሃ እቀባ ሥራ ይከናወናል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 8/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተቀናጀ የአፈር እና ውሃ እቀባ ስራዎች እንደሚከናወኑ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአማራ ክልል የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የመስኖና የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ልቼ ቀበሌ ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ስራ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ካልመጣ የመስኖ ስራ ውጤታማ እንደማይሆን ገልጸዋል።
ክልሉ በመስኖ መልማት የሚችል ሰፊ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ በዚህ ዓመት ከ52 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአዲስ መስኖ በማስገባት የክልሉን የመስኖ ልማት ወደ 383 ሺህ ሄክታር ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ከተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ስራዎች አንጻርም በዚህ ዓመት ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈር እና ውሃ እቀባ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
ይህንንም ለማድረግ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የሚሆን የደን እና የፍራፍሬ ችግኝ ልማት እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዝግጅቶቹ የመስኖ አውታር ግንባታ፣ የቅየሳ፣ የአርሶ አደሮች ስልጠና እንዲሁም የችግኝ ጣቢያዎች ግንባታ እና የእርሻ መሳሪያ ዝግጅቶችን ያካተተ መሆኑን አንስተዋል።
በተደረጉ ጥናቶች ክልሉ በመስኖ ሊለማ የሚችል 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዳለው ገልጸዋል።
ይህንን ለማልማትም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ረገድ ባለፉት ዓመታት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በርካታ የውሃ መሳቢያ መሳሪያዎች ወደ ዞኖች እና ወረዳዎች መከፋፈሉን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ስራ መሆኑን ገልጸዋል።