አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የአህጉሪቱን ወጣቶች የፈጠራ አቅም ማጎልበት ይገባል - ምክትል ሊቀ-መንበር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ - ኢዜአ አማርኛ
አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የአህጉሪቱን ወጣቶች የፈጠራ አቅም ማጎልበት ይገባል - ምክትል ሊቀ-መንበር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ):- የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት ቴክኖሎጂና ፈጠራን ከአጀንዳ 2063 ጋር ማቀናጀትና የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ማጎልበት እንደሚገባ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ ገለጹ፡፡
የአፍሪካ ህብረት የኢኖቬሽን ፌስቲቫል በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ፌስቲቫሉ "የአፍሪካ ህብረት ወጣቶችን የአህጉራዊ ኢኖቬሽን መሪ የማድረግ ተግባር" በሚል ርዕሰ ጉዳይ የሚካሄድ ሲሆን ኢኖቬተሮች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የግሉ ዘርፍ መሪዎች እና የወጣት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ፌስቲቫሉ ለሀገር በቀል የኢኖቬሽን መፍትሄዎች እውቅና በመስጠት ስራዎችን የበለጠ ማላቅ ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ ፈጠራንና ቴክኖሎጂን ከአጀንዳ 2063 ጋር በማቀናጀት የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት መትጋት ይገባል ብለዋል፡፡
አፍሪካን ለመለወጥና ለማሳደግ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ፈጠራን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአህጉሪቱ የፈጠራ ችሎታ፣ የዲጂታል ለውጥ እና የሥራ ፈጠራ ዋና አንቀሳቃሽ ኃይሎች ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አህጉሪቱ በፈጠራ ዘርፍ የያዘችውን ግብ ማሳካት የሚችሉት ወጣቶች በመሆናቸው አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሴቶች፣ የጾታ እና ወጣቶች ዳይሬክተር ፕሩደንስ ንግዌንያ በበኩላቸው ወጣቶችና ሴቶች የአፍሪካን የፈጠራ ምህዳር መሠረት መጣል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
አፍሪካ በፈጠራ ዘርፍ ማሳካት የምትፈልገውን ለውጥ እውን ለማድረግ በወጣቶችና ሴቶች የፈጠራ አቅም ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ወጣት ትመር ብርሃኔ አፍሪካዊያን በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ዘርፍ ያለንን ዕውቀት በየጊዜው ማላቅ አለብን ስትል ተናግራለች፡፡
ወጣት አሜን ቢኒያም በበኩሏ የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ ፈጠራን እና ቴክኖሎጂን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን ጠቅሳ ለዘርፉ የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር የተያዘው ግብ ስኬታማ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝባለች፡፡
የኢኖቬሽን ፌስቲቫሉ እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት፣ አካታችና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ራዕይ አቀጣጣይ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡