የአፍሪካ የግብርና፣ ውሃ እና ከባቢ አየር አጀንዳ፤ እድሎች እና ፈተናዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የግብርና፣ ውሃ እና ከባቢ አየር አጀንዳ፤ እድሎች እና ፈተናዎች

አፍሪካ ዘላቂ ልማትን ለማሳካትና እንድትበለጽግ የጀመረችው ጉዞ ወሳኝ መዕራፍ ላይ ይገኛል። የአህጉሪቱን የመለወጥ ትልም ባሏት እምቅ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ላይ የተመረኮዘ ነው። ተዝቆ የማያልቀው የአፍሪካ ብዝሃ ሀብት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግና አይበገሬ አቅም መገባንት የሚያስችሏትም ጭምር ናቸው።
ግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የውሃ ሀብቶቿ እና ብዝሃ ከባቢ የአየር ንብረቷ ከሀብቶቿ መካከል ይጠቀሳሉ።
ግብርና አሁንም የአፍሪካ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። ዘርፉ ለአህጉሪቱ 35 በመቶ የሚጠጋ አጠቃላይ ጥቅል ሀገራዊ ምርት(ጂዲፒ) አስተዋጽኦ ያደርጋል። 60 በመቶ ህዝብም በግብርና ስራ እንደሚተዳደር የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) ሰነድ ያሳያል። ከዚህም ውስጥ አብዛኞቹ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ናቸው።
ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ካለው የሰው ኃይል የ50 በመቶ ድርሻው ይወስዳሉ። የአፍሪካ ህዝብ 60 በመቶ ድርሻ የያዘው ወጣት በግብርና ንግድ፣ እሴት መጨመርና የኢኖቬሽን ስራዎች ያለው ተሳትፎ እያደገ መጥቷል። የዓለም 60 በመቶ ያልለማ መሬት ያለው በአፍሪካ ነው። ሰፊ የውሃ ሀብቶችና እያደገ ያመጣው ብሉ ኢኮኖሚ(የባህር እና ሌሎች የውሃ ሀብቶች) ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ እድገትን የሚያረጋግጡ ናቸው።
የመሰረተ ልማቶች ተደራሽነት ማደግ፣ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶችና ኢኖቬሽንን የተመረኮዙ የፋይናንስ አማራጮችን መስፋት ግብርናን የምግብ ምንጭ ብቻ ሳይሆን ለኢንዱስትሪ ልማት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ንግድ መሳለጥ ትልቅ አቅም መሆን ይችላል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በግብርና ምርቶችና አገልግሎቶች ያለውን አህጉራዊ የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው። የንግድ ቀጣናውን በሚገባ መጠቀም ከተቻለ እ.አ.አ በ2030 የግብርና ንግድ ልውውጡን በ30 በመቶ ማሳደግ እንደሚቻል ጥናቶች ያመለክታሉ።
ግብርናው የተጠቀሱት ጥንካሬዎች ያሉት ቢሆንም ረጅም ጊዜ የዘለቁ መዋቅራዊ ፈተናዎች አብረውት ዘልቀዋል።
የግብርና ምርቶች ላይ የሚፈለገውን ያህል እሴት አለመጨመር፣ የቴክኖሎጂ አጠቀቃምና የምርታማነት ውስንነት፣ የመሰረተ ልማቶች እና ሎጅስቲክስ በበቂ ሁኔታ አለመሟላት፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ክፍተቶች ከአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንዲሁም እያደገ ከመጣው ህዝብ ጋር ተዳምሮ ግብርናውን እየፈተነው ይገኛል።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ማጠንጠኛ የሆነው ጉዳይ የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት(ካዳፕ) ነው። እ.አ.አ በ2003 የአፍሪካ ህብረት በሞዛምቢክ ባደረገው ስብሰባ የግብርና የምግብ ዋስትና ድንጋጌን አጽድቋል። ይህ ማዕቀፍ የማፑቶ ድንጋጌ ስያሜን በማግኘት የካዳፕ ትግበራ በይፋ እንዲጀመር አድርጓል።
የማፑቶ ድንጋጌ እ.አ.አ በ2014 በማላቦ ድንጋጌ (ከእ.አ.አ 2014 እስከ 2025 የተተገበረ) በአዲስ መልክ የታደሰ ሲሆን የተለያዩ ቃል ኪዳኖችን በውስጡ ይዟል። ይህም በካዳፕ አማካኝነት የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ከአጠቃላይ ዓመታዊ ጥቅል ምርታቸው(ጂዲፒ) ቢያንስ ስድስት በመቶውን ለግብርናው ዘርፍ እንደሚመድቡና በየሀገራቱ በዘርፉ በየዓመቱ በአማካይ ስድስት በመቶ እድገትን የማሳካት ግብ አለው።
ረሃብን ማጥፋት፣ ድህነትን በግማሽ መቀነስ፣ የማይበገር አቅም መገንባትና የጋራ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ሌሎች ግቦች ናቸው።
ካዳፕ የአፍሪካ ሀገራት በስርዓተ ምግብ ያላቸውን ኢንቨስተመንት በማሳደግ፣ በአፍሪካ የእርስ በእርስ የግብርና ንግድን በማሳደግና የፖሊሲ መሰናሰልን በመፍጠር ቁልፍ ሚና ተወጥቷል። ይሁንና የተመዘገቡት ውጤቶች ያልተመጣጠነ ልዩነት የሚታይባቸው ናቸው። የ2023 የካዳፕ የግምገማ ሪፖርት እንደሚያሳየው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የማላቦ ግቦችን ማሳደግ የሚያስችል መንገድ ላይ እንዳልሆኑ ያስቀምጣል። ይሁንና 26 ሀገራት በተቀመጡ ግቦች መመዘኛ መሻሻል እንዳሳዩ ይገልጻል።
ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ካሜሮን፣ ግብጽ፣ ማሊ፣ ጋና እና ጋምቢያ የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹ ሀገራት በግብርና ኢንቨስትመንት፣ ምርታማነት እና የፖሊሲ ትግበራ ላይ ፈተናዎች እንዳሉበት ሪፖርቱ አመልክቷል። ሀገራት የሰነዱን ትግበራ ማፋጠንና ተቋማዊ ቅንጅትን ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስቧል።
የማላቦ ድንጋጌ ወደ መገባደዱ ላይ የሚገኝ ሲሆን የካዳፕ ቀጣዩ ምዕራፍ የካምፓላ ድንጋጌ ነው። ይህ የትግበራ ምዕራፍ ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2035 የሚቆይ ነው። የካምፓላ ድንጋጌ ከማፑቶ እና ማላቦ ድንጋጌዎች ትምህርቶችን በመውሰድ የግብናውን እድገት ማላቅ ግቡ አድርጎ ይዟል።
የካምፓላ አጀንዳ ኢኖቬሽን፣ ዲጂታላይዜሽን፣ አረንጓዴ እድገት እና አይበገሬነት ያላቸውን ሚና በማንሳት መስኮቹ ስርዓተ ምግብን ዘላቂና አካታች የማድረግ ግብን ማሳካት እንደሚያስችሉ አመልክቷል።
በዚህ ማዕቀፍ እ.አ.አ 2050 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ህዝብ ይኖራታል ተብሎ የሚጠበቀውን አፍሪካን በራስ አቅም የመመገብ ውጥን የያዘ ነው።
ይሁንና የግብርና ምርታማነት ከዓለም አቀፍ አማካይ የምርታማነት ምጣኔ አንጻር ሲታይ አሁንም ወደ ኋላ ቀረት ያለ ነው። ይህም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች የተገደበ የፋይናንስ አቅርቦት ማግኘታቸው እንዲሁም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው አለመደረጉ የችግሩ አብይ መንስኤ ሆኖ ይጠቀሳል። የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችና የከባቢ አየር ብክለት ፈተናዎቹ እንዲበረቱ አድርጓል።
ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ የበይነ መንግስታት ፓናል(IPCC) አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እርምጃዎችን በፍጥነት ካልወሰደች እ.አ.አ በ2050 የግብርና ምርታማነቷ ከ20 እስከ 30 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ገምቷል። ከ250 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን ደህንነቱ ያልተረጋገጠ እና ንጽህናው ያልተጠበቀ የውሃ አቅርቦት ፈተና ውስጥ ይገኛሉ።
በህዝብ ቁጥር መጨመር፣ በከተሜነትና ኢንዱስትሪ መስፋፋት ምክንያት ንጹህ የውሃ አቅርቦትን የማግኘት ጉዳይ የበለጠ ሊስፋ እንደሚችል ተመላክቷል።
የአፍሪካ ህብረት የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩና ፈተናዎች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ለአባል ሀገራት የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።
የህብረቱ የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር የስራ ክፍሉ(DARBE) አማካኝነት የአፍሪካን ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና ኢኒሼቲቮች የተናበቡና የጋራ ግብ ያላቸው እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል። የአቅም ግንባታ፣ የቴክኒክ እና የፖሊሲ ድጋፍም የሚያደርግ ሲሆን ብሄራዊ እቅዶች ከአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ሰነዶችና የአጋርነት ማዕቀፎች ጋር የተጣጠሙ መሆናቸውን ያረጋገጣል።
የስራ ክፍሉ ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ የግሉ ዘርፍና የልማት አጋሮች ጋር አጋርነቶችን የማጠናከር ስራ ያከናውናል። ግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ አስተዳደር፣ የአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነት እንዲሁም የተፈጥሮ እና የብሉ ኢኮኖሚ ሀብቶች በዘላቂነት መጠቀም ላይ የተቀናጁ አሰራሮችን መፍጠር ላይም ይሰራል።
የዘርፉ አጠቃላይ ስራዎች አካል የሆነው ስድስተኛው የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል።
በስብሰባው ላይ ሚኒስትሮች፣ ባለሙያዎችና የልማት አጋሮች ይሳተፋሉ።
የአፍሪካ የግብርና ኢኒሼቲቮች አፈጻጸም መገምገምና ዘርፉ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከር የስብሰባው አላማ ነው።
እ.አ.አ በ2023 በአዲስ አበባ የተካሄደውን አምስተኛው የልዩ ኮሚቴ ስብሰባ ውጤቶች ግምገማ ይደረጋል።
የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም(ካዳፕ) የማላቦ ድንጋጌ(ከእ.አ.አ 2014 እስከ 2025) ስኬቶች እና የካዳፕ የካምፓላ ድንጋጌ (ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2035) አፈጻጸም ላይ ውይይት ይካሄዳል።
የስርዓተ ምግብን ማጠናከር፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ምርታማነት ስርዓት መዘርጋት፣ የበካይ ጋዞችን ልህቀት መቀነስና ዘላቂ የውሃና የተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደርን ማጠናከር ሌሎች የምክክር አጀንዳዎች ናቸው።
በአፍሪካ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ዘላቂ እድገትን ማምጣት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክረ ሀሳቦች ይቀርባሉ።
ውይይቱ እ.አ.አ በ2026 በአዲስ አበባ የሚካሄዱትን የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባና የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚሆኑ አጀንዳዎችን እንደሚያዘጋጅ ተመላክቷል።
የአፍሪካ ህብረት ግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር አጀንዳ 2063 ለማሳካት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ዘርፎች መሆናቸውን አመልክቷል። ህብረቱ የግብርና እና የገጠር ልማት የበለጠ ማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክቷል።
የህብረቱ አባል ሀገራት የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራምን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲተገብሩም ጥሪ አቅርቧል።
ስድስተኛው የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ውሃ እና ከባቢ አየር ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ጥቅምት 11 እና 12 እንዲሁም ጥቅምት 14 በሚኒስትሮች ደረጃ እንደሚያከናውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አፍሪካ ወደ ዘላቂ ግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ውሃ አስተዳደር እና አካባቢ ጥበቃ እያደረገች ያለው ጉዞ አንገብጋቢ አጀንዳና ሽግግሩን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና አለው። አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የፋይናንስ ማነቆ፣ መሰረተ ልማቶች እና የፖሊሲ የመፈጸም አቅም ውስንነትን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች ቢኖሩባትም እድሎቿ ፈርጀ ብዙ ናቸው። በርካታ ያልለማ መሬት፣ ሰፊ የውሃ ሀብት፣ ወጣቶች እና የብሉ ኢኮኖሚ ሀብቶች በአፍሪካ ዘላቂ የግብርና እድገት ለማረጋገጥና ሁሉን አቀፍ ስርዓተ ምግብ ለመገንባት የሚያስችል ነው።
ለአርሶ አደሮች በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግን ጨምሮ አቅማቸውን መገንባት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ሀገራት ብሄራዊ ፖሊሲዎቻቸውን ከአህጉራዊ ማዕቀፎች ጋር ማጣጣም ይኖርባቸዋል። ግቦችን ለማሳካት የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋት ይገባል። የተፈጥሮ ሀብትን በሚገባ መጠቀም፣ በኢኖቬሽን ላይ መዋዕለ ንዋይን ፈሰስ ማድረግና አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች፣ አረንጓዴ እና የበለጸገች አህጉር መገንባት ይቻላል።