ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለምን አስፈለጋት? - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግር ለምን አስፈለጋት?

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቲኒዮ ጉቴሬዝ አነሳሽነት እ.አ.አ 2021 የተመድ የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በኒው ዮርክ በበይነ መረብ አማራጭ ተካሄዷል።
“የህዝቦች ጉባኤ” እና “የመፍትሄ ጉባኤ” የሚሉ ስያሜዎች የተሰጠው ጉባኤ ላይ ከ193 ሀገራት የተወጣጡ ከ51 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል።
በምግብ ስርዓት ላይ የተዘጋጀ ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ዓለም አቀፍ ሁነት ዋንኛ ግቡ የነበረው የተመድ አባል ሀገራት የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን እንዲያመጡ እና ስርዓተ ምግብን ከዘላቂ ልማት ግቦች በተለይም ከግብ ሁለት ረሃብን ማጥፋት ጋር ማስተሳሰር ነው።
ጉባኤው በአምስት ዓበይት የትኩረት ነጥቦች ላይ ያተኮረ ነበር።
ለሁሉም ዜጋ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽ ማድረግ፣ ከብክነት ወደ ዘላቂ የምግብ አጠቃቀም መሸጋገር፣ ተፈጥሮን ያማከለ የምግብ ምርማነትን ማሳደግ፣ እኩልነትን መሰረት ያደረገ የአኗኗር ሁኔታን ማጠናከር እና ለአደጋዎችና ጫናዎች የማይበገር ጠንካራ የምግብ ስርዓት መገንባት ጉባኤው የተወያየባቸው ጉዳዮች ናቸው።
ጉባኤው በወቅቱ አባል ሀገራት ሁሉን አቀፍ የምግብ ስርዓትን በመፍጠር የዘላቂ ልማት ግቦችን እንዲያሳኩ ጥሪ አቅርቧል።
የተመድ የዓለም የምግብ ደህንነት ኮሚቴ የምግብ እና የስነ ምግብ ከፍተኛ የባለሙያዎች ፓናል የስርዓተ ምግብ አካሄድ ከባቢ አየር፣ ዜጎች፣ ግብአቶች፣ ሂደቶች፣ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን ጨምሮ ሁሉንም ተዋንያን ያሳተፈ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል።
ስርዓተ ምግብ ምርት፣ ማቀነባበር፣ ስርጭት፣ ማዘጋጀት፣ መመገብ እና የተረፈ ምግብ አወጋገድን አቅፎ የያዘ እና ይህም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ከባቢ አየር ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያለው ነው።
የባለሙያዎች ፓናሉ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ዜጎች፣ ምድር፣ ብልጽግና፣ ሰላም እና አጋርነት ላይ ያውጠነጠነ መሆኑን ይገልጻል።
ፓናሉ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በምግብ ስርዓት ላይ ለውጥ ያመጣል ያላቸውን ስድስት ሀልዮታዊ ማዕቀፎችን ቀርጿል።
ህይወት ያላቸው እና የቁስ አካላት ባህርያት፣ ከባቢ አየር የመጀመሪያው ነው። በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና መሰረተ ልማት ሲሆን ኢኮኖሚ እና ገበያ ሶስተኛውን ስፍራ ይይዛል።
ፖለቲካ እና ተቋማዊ ሁኔታ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች እንዲሁም የስነ ሕዝብ ውቃሬ ሌሎች የምግብ ስርዓት ለውጥ አምጪ ምክንያቶች እንደሆኑ ተቀምጧል።
ስድስቱ የምግብ ለውጥ አሳላጭ ሁኔታዎች ተፈጻሚ እና ውጤታማ የሚያደርጉ አራት ቁልፍ መስኮች እንዳሉም የባለሙያዎች ፓናሉ ያስቀምጣል።
የምግብ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ስርዓቶችን መደገፍ፣ የምግብ አቅርቦት ሰንሰለትን ማጠናከር፣ የዜጎችን የምግብ አጠቃቀም ባህሪያት ላይ ለውጥ ማምጣት እና የተመጣጠኑ ንጥረ ምግቦችን ብዝሃነት ማስፋት ቁልፍ የትኩረት ጉዳዮች ናቸው።
የተቀመጡትን ማዕቀፎች፣ ለውጥን የመፍጠሪያ መንገዶች እና አስቻይ ሁኔታዎች ከፖሊሲ እና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር ጋር በማቆራኘት የምግብ ስርዓት ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚገቡ ባለሙያዎቹ ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ።
የኢትዮጵያ የስርዓት ምግብ ራዕይ (EFS) መነሾም በስርዓተ ምግብ ጉባኤው እ.አ.አ በ2030 መሳካት አለባቸው ብሎ ያስቀመጣቸውን የስርዓተ ምግብ ግቦች እውን ለማድረግ ያሉ ፈተናዎች እና እድሎች ናቸው።
እ.አ.አ በ2024 የወጣው የኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሁሉን አቀፍ ሪፖርት ኢትዮጵያ በጉባኤው የተቀመጡ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እና የጉባኤውን ምክረ ሀሳቦች ለመተግበር ቁርጠኛ እንደሆነች ይገልጻል።
የኢትዮጵያ መንግስት እ.አ.አ ዲሴምበር 2020 የኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ የአሰራር ሂደት ይፋ ያደረገ ሲሆን ሂደቱ እ.አ.አ ጃንዋሪ 2021 ተጀምሯል።
የስርዓተ ምግብ ማዕቀፉ የኢትዮጵያን የስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ራዕይን በግልጽ ያስቀመጠ ነበር።
በወቅቱ ሂደቱን ለማስጀመር የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን እና የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የመሯቸው የከፍተኛ ደረጃ ምክክሮች የተደረጉ ሲሆን ሰነዶችም ተቀርጸዋል።
በስርዓት ምግብ ላይ ሁለት ብሄራዊ ምክክሮች የተደረጉ ሲሆን ምክክሮችን ተከትሎ የኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ ሂደት ይፋ ሆኗል።
ምክክሮቹ የኢትዮጵያ ምግብ ስርዓት አሁናዊ ሁኔታ አና መጻኢ ሁኔታዎች፣ የኢትዮጵያን የምግብ ስርዓት የመለወጥ ጉዞ በሚል ርዕስ የተካሄዱ ናቸው።
የስርዓተ ምግብ ሂደት ቀረጻው ላይ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህረሰቦች፣ የምርምር ተቋማት፣ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ተቋማት ያሉባቸው ከ120 በላይ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ይፋ የሆነውም የስርዓተ ምግብ ሂደት ሰነድ እ.አ.አ በ2021 በጣልያን ሮም በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ላይ ቀርቦ አዎንታዊ ምላሾችን አግኝቷል።
የስርዓተ ምግብ ሂደት ማዕቀፉ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ፣ ከ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ እንዲሁም ከሌሎች የፖሊሲ እና አሰራሮች ጋር የተጋመደ ነው።
የኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሁሉን አቀፍ ሪፖርት ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ለውጥ እና ሽግግር ያስፈለገባቸውን ምክንያቶች ያስቀምጣል።
የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ተደራሽነት በሚፈለገው ደረጃ ማረጋገጥ አለመቻል፣ ፈጣን የህዝብ እድገት፣ የክትመት መጠን መስፋፋት፣ የከባቢ አየር ጉዳት እና የአየር ንብረት ለውጥ፣ እኩል ያልሆነ የዜጎች አኗኗር፣ ደካማ የምግብ ስርዓት መሰረት፣ ግብርናን ለኢኮኖሚ ያለውን ድርሻ ማሳደግ እና የምግብ ስርዓትን ከብሄራዊና ዓለም አቀፍ ግቦችን ጋር ማሰናሰን ማስፈለጉ የስርዓተ ምግብ ለውጡ መሰረታዊ ለውጥ መነሻ ናቸው።
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ሽግግር ውስጥ ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የንጥረ ነገሮችን ብዝሃነት በማስፋት፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ተደራሽነትን በማሳደግ እና የግብርና ማቀነባበሪዎችን ቁጥር በመጨመር አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግባለች።
በዚህም በዜጎች ጤና እና ገቢ እድገት ላይ ለውጦች መምጣታቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።
ብሄራዊ የምግብ ስርዓት ማዕቀፎች፣ በምክክሮች የዘርፉ ተዋንያን የማሳተፍ ሁኔታ እያደገ መምጣት፣ በምግብ ስርዓቱ በሰባቱ ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ስር ለውጥ አምጪ ተብለው የተቀመጡ 24 መፍትሄዎች እና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ሌሎች የታዩ አበረታች ለውጦች ናቸው።
ሰባቱ ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ፣ ጤናማ የአመጋገብ ሁኔታን መፍጠር፣ አሰራሮች እና ፖሊሲዎችን በተቀናጀ መንገድ መተግበር፣ በምግብ ስርዓቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና አሰራሮችን መተግበር፣ የገበያ ተደራሽነት ማስፋት እና መረጃ አሰጣጥን ማጠናከር፣ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎችን መጠበቅ እና የማይበገር አቅም መገንባት እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ ዘላቂነት ያለው የከተሜነት እድገትን መፍጠር እና ክህሎት ልማት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በሚፈለገው መጠን ተደራሽ አለማድረግ፣ ደካማ የምግብ ደህንነት መሰረተ ልማት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አለመስፋፋት፣ የከባቢ አየር ጉዳቶች፣ የቅንጅታዊ አሰራር ላይ ያሉ ክፍቶች እና የዜጎች የአኗኗር ሁኔታ ለይ ለውጦች ቢኖሩም አመርቂ አለመሆን፣ የፋይናንስ ውስንነት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽነት በምግብ ስርዓቱ ዋና ፈተናዎች ተብለው የተቀመጡ ናቸው።
የምግብ ስርዓትን አስተዳደርን እና የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን ማጠናከር፣ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ መዋቅሮችን መዘርጋት፣ የመንግስት እና የግል አጋርነትን ማጠናከር፣ አቅምን መገንባት እና የምግብ ስርዓት አጀንዳ ዘላቂነት ባለው እና በተቀናጀ ሁኔታ ለማህበረሰቡ ማስገንዘብ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ተብለው ከተለዩ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።
የገበያ ትስስርን ማጠናከር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዶች እና ስትራቴጂዎችን ማቀናጀት እንዲሁም ወጣቶች፣ ሴቶች እና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ የስርዓተ ምግብ ትግበራው ሁሉን አካታችነት የበለጠ ማረጋገጥ ቀጣይ የቤት ስራ ተብለው የተያዙ ናቸው።
በአጠቃላይ የስርዓተ ምግብ ማዕቀፉን በየጊዜው በመፈተሽ እና የሁኔታዎችን ተለዋዋጭነት ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ የአስተዳደር መዋቅርን በማሻሻል እ.አ.አ በ2030 የተያዙ ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ሁሉን አቀፍ ሪፖርቱ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በስርዓተ ምግብ ላይ እያከናወነች ያለውን ስራ ለዓለም የማሳወቅ ስራ ታከናውናለች።
በስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ያላትን ተሞክሮዎች በዋናው ጉባኤ እና በጎንዮሽ ሁነቶች ላይ ታቀርባለች።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያን የስርዓተ ምግብ የተግባር ስራዎች እና ውጤቶች በመስክ ምልከታቸው ይቃኛሉ።