ቀጥታ፡

ማድያት እና ህክምናው

ማድያትን ለማከም አስቸጋሪ መሆኑንና በታካሚዎች ላይም የሥነ ልቡና እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊያመጣ የሚችል መሆኑን የቆዳ ሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ስለ ማድያት መንስዔ፣ ስለሚከሰትበት የሰውነት ክፍል፣ ማድያት ያለበት ሰው ማድረግ ስላለበት ጥንቃቄ፣ ቆዳን ስለሚያስቆጣ ሠርካዊ ልማድ እና ሕክምናውን በተመለከተ በራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል የቆዳ እና አባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ዶክተር አደራጀው ብርሃን ከኢዜአ ቆይታ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም፤ በቆዳ ውስጥ ያሉ ቀለም አምራች ኅዋሶች(ሴሎች) ከመጠን በላይ ቀለም ሲያመርቱ ማድያት ተከሰተ እንደሚባል ገልጸዋል። 

ለዚህም መንስዔው የተፈጥሮ ተጋላጭነት ከተለያዩ ቀስቃሽ ምክንያቶች ጋር የሚያደርጉት መሥተጋብር መሆኑን አስረድተዋል።

👉 የማድያት መንስዔ ምንድን ነው?

1ኛ. የሆርሞን ለውጥ፡- በእርግዝና ወቅት ወይም የወሊድ መቆጣጠሪያ ሲጠቀሙ የሚኖር የሆርሞን ለውጥ ማድያት እንዲከሰት ወይም እንዲባባስ ያደርጋል ይላሉ የሕክምና ባለሙያው።

2ኛ. የፀሐይ ጨረር፡- ከልክ ያለፈ ፀሐይ ቀለም አምራች ኅዋሶች(ሴሎች) በብዛት ቀለም እንዲያመርቱ ስለሚያነቃቃ፤ የፀሐይ ጨረር ዋነኛ ቀስቃሽ እና አባባሽ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።

3ኛ. የዘር ሐረግ፡- በቤተሰብ ውስጥ ማድያት ካለ በዘር የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ይናገራሉ።

4ኛ. የቆዳ ዓይነት፡- ጥቁሮች (ከቡናማ እስከ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው) ንቁ ቀለም አምራች ሴሎች ስላሏቸው ለማድያት የሚኖራቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

5ኛ. ሌሎች መንስዔዎች፡- ሙቀት (የሚታዩ እና የማይታዩ ጨረሮች እንዲሁም የምድጃ እሳት)፤ የተለያዩ መድኃኒቶችና የመዋቢያ ምርቶች፤ የእንቅርት ዕጢ ህመሞች እንዲሁም ጭንቀት ማድያት እንዲከሰት ወይም እንዲባባስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውንም የሕክምና ባለሙያው አስገንዝበዋል።

👉 ማድያት በየትኛው የቆዳ ክፍል ላይ ይከሰታል?
ማድያት ከሚከሰትበት የቆዳ እና የሰውነት ክፍሎች አንጻር በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ዶክተር አደራጀው አንስተዋል። እነሱም

1ኛ. ከሚከሰትበት የቆዳ ክፍል አንጻር፡- ማድያት በውስጠኛውም ሆነ በላይኛው የቆዳ ክፍሎች ላይ ወይም በሁለቱም ላይ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።

2ኛ. ከሚከሰትበት የሰውነት ክፍሎች አንጻር፡- የሕክምና ባለሙያው እንዳሉት 60 በመቶ ማድያት ግንባር፣ ጉንጭ፣ አፍንጫ፣ የላይኛው ከንፈር እና አገጭ ላይ ይከሰታል ብለዋል።
30 በመቶው ደግሞ ጉንጭ እና አፍንጫ ላይ እንዲሁም 10 በመቶው የአገጭ መስመርን ተከትሎ እንደሚከሰት አስረድተዋል።

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ከፊት የሰውነት ክፍሎች በተጨማሪ በደረት፣ አንገት እና ክንድ ላይ የሚከሰትበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።
👉 የማድያት ባሕርይ

ማድያት የቆዳ ቀለም ለውጥ ያመጣል፤ በግራና በቀኝ የፊት ክፍል ይወጣል። የማሳከክ ወይም የህመም ስሜት እንደሌለውም ዶክተር አደራጀው አስረድተዋል።

•  ማድያት በላይኛው የቆዳ ክፍል ላይ ሲከሰት፡- ነጣ ወይም ጠቆር ያለ ቡናማ የሆነ የቆዳ ቀለም ለውጥ እንደሚያሳይ አመላክተዋል።

•  ማድያት በውስጠኛው የቆዳ ክፍል ላይ ሲከሰት፡- ሰማያዊ ግራጫ ወይም ጠቆር ያለ ግራጫ የቆዳ ቀለም ለውጥ እንደሚያሳይ አንስተዋል።

• ማድያት በሁለቱም የቆዳ ክፍሎች ላይ ሲከሰት፡- የተቀላቀለ የቡናማ እና ግራጫ ቀለም ለውጥ እንደሚያሳይም ባለሙያው አብራርተዋል።

👉 ማድያት ያለበት ሰው ምን ዓይነት ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይገባዋል?

1ኛ. ወርቃማ ጥንቃቄ፡- 

• ተከታታይና ጥብቅ የሆነ የፀሐይ መከላከያ መጠቀም ይገባል ይላሉ የሕክምና ባለሙያው። በዚህም መሠረት ከቤት ከመውጣት ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ቀደም ብሎ የፀሐይ መከላከያ ክሬሞችን መቀባትና በሁለት ሠዓት ልዩነት እየደረቡ መቀባት። 

• በሌላ በኩል ከ4 እስከ 10 ሠዓት ያለው የፀሐይ ሙቀት ለቆዳ ህመም አጋላጭ መሆኑን በመገንዘብ ከፀሐይ መከላከያ ክሬም በተጨማሪ ጥላና ኮፍያን መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል።   

2ኛ. ቆዳን የሚያስቆጣ የቆዳ እንክብካቤ (መስተካከል ያለበት ልማድ)•  ቆዳን የሚያስቆጡ መታጠቢያዎች(ሳሙናን ጨምሮ ሌሎችም) እንዲሁም መዋቢያዎችና የሚቀቡ ነገሮች (ኮስሞቲክስን ጨምሮ ሌሎችም) አለመጠቀም ይገባል ይላሉ።  

•  ለቆዳ ተስማሚ የሆኑ ማለስለሻዎችን በደንብ መጠቀም እንደሚገባም ይመክራሉ። 

3ኛ. በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም
• በሐኪም የታዘዘ መድኃኒትን በአግባቡ(ሳያቆራርጡ) መጠቀም እንደሚመከር ያስረዱት ዶክተር አደራጀው፤ እንደ ማድያቱ እና እንደ ሰዎቹ ቆዳ ዓይነት መድኃኒቱ ለውጥ የሚያሳይበት ጊዜ ስለሚለያይና ከ8 እስከ 12 ሣምንት ሊወስድ ስለሚችል ታግሶ በደንብ ቢጠቀሙ መልካም ነው ይላሉ።

4ኛ. የተለያዩ የሕክምና አማራጮችን መጠቀም•  የሕክምና ባለሙያው እንደሚመክሩት፤ በዘርፉ ያሉ የተለያዩ የሕክምና ዓይነቶችን ለምሳሌ እንደ ኬሚካል ፒልስ፣ የቆዳ ሕክምና እና ማይክሮ ኒድሊንግ ያሉትን በሐኪም ምርመራ መሠረት መጠቀም ይገባል።
5ኛ. ከወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የተከሰተ ማድያት ከሆነ ከሕክምና ባለሙያ ጋር በመመካከር ሌላ አማራጭ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል። እንዲሁም ጭንቀትን መቀነስ እንደሚገባ መክረዋል።

👉 የማድያት ሕክምናን በተመለከተ
የማድያት ሕክምና በጣም አስቸጋሪ ከሚባሉትና ረጂም ጊዜ ከሚወስዱ እንዲሁም በመመላለስ ከሚያስቸግሩ የቆዳ ሁኔታዎች አንዱ መሆኑን ዶክተር አደራጀው ገልጸዋል።

በሕክምና ማድያቱ የጠፋላቸው ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠው፤ በሌላ በኩል በሕክምና ሂደት የማድያቱ ሁኔታ ከነበረበት እየቀነሰ ለውጥ የሚታይበት ሁኔታ አለ ብለዋል።

ይህን ለውጥ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ማስቀጠል እንደሚገባም ይመክራሉ። እንክብካቤው ከተቋረጠ ግን ማድያቱ እንደገና የሚመለስበት ሁኔታ መኖሩን አስገንዝበዋል።

👉 የማድያት ሕክምና አማራጮች
የሚቀቡ መድኃኒቶች፣ የሚዋጡ መድኃኒቶች፣ ሌሎች የሕክምና አማራጮች(ኬሚካል ፒልስ፣ የቆዳ ሕክምና እና ማይክሮ ኒድሊንግ)፣ የፀሐይ መከላከያ አማራጮችን በአግባቡ አዘውትሮ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም