አምራች ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ሚናውን እንዲወጣ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ሚናውን እንዲወጣ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦አምራች ኢንዱስትሪው በሀገራዊ እድገት ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች እና አባላት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ጎብኝተዋል።
በተጨማሪም የምክር ቤቱ አመራሮች እና አባላት የ ኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጉብኝቱ የኢንዱስትሪዎቹን የስራ እንቅስቃሴ እና ያሉበትን ደረጃ ለመመልከት ዓላማ ያደረገ ነው።
ዕሴት የተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ እና በብረታ ብረት ምርት ላይ የተሰማራው ኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝት የተከናወነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥሪ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
አፈ ጉባኤው በጉብኝታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ራዕይ ያለው ምን መፍጠር እንደሚችል ተመልክተንበታል ብለዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
የአምራች ዘርፉ የውጭ ምንዛሪን በማዳን እና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል።
ምክር ቤቱ የዘርፉን እድገት የሚያረጋግጡ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻሉን ጠቅሰው፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚደረግላቸው ክትትል እና ድጋፍ ተጠናክረው እንዲወጡ ይሰራል ብለዋል።
የዘርፉን እድገት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበው፤ለዚህ ደግሞ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ በበኩላቸው መንግስት ብዝሀ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ እና ሀገርን ለማበልጸግ ከያዛቸው ዘርፎች አንዱ ኢንዱስትሪ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝታቸውም የሚያበረታታ ስራ መመልከታቸውን ጠቅሰው አፈጻጸሙ ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም እንደ ሀገር የእድገት፣ የብልጽግና እና የማንሰራራት ጉዟችን በትክክለኛው መስመር ላይ እንደሚገኝ ለመመልከት ችለናል ብለዋል።
ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም ተሞክሮውን በመጋራት አካባቢ፣ ዜጋንና ትውልድን ለማሻገር መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ በሁለንተናዊ መልኩ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የኢንዱስትሪ እድገት የሚረጋገጠው በቅንጅታዊ ጥረት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ናቸው።
ለማደግና ለመበልጸግ የእድገት መስመሩ ኢንዱስትሪ መሆኑን ጠቅሰው ምክር ቤቱ ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የጀመረውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲረጋገጥና የዘርፉ ተወዳዳሪነት እንዲጨምር በኢንዱስትራላይዜሽን ላይ የተጀመረው ርብርብ በሁሉም አቅጣጫ መጠናከር አለበት ብለዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ