የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ሚናው የጎላ ነው - ቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ሚናው የጎላ ነው - ቱሪዝም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ በዚህ ዓመት የሚጸድቀው የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት የዘርፉን ዕድገት ለማስቀጠል ሚናው የጎላ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገለጹ።
የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት ተጠናቆ ለሚመለከተው አካል እንዲጸድቅ መላኩንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ከአለም ሀገራት በቀዳሚነት የሚያስቀምጧት በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሏት ይታወቃል፡፡
ቱሪዝም ከአምስቱ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ አንዱ በመሆኑ ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ ከዚህ ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ ማሻሻያ እየተደረገበት ነው፡፡
አዲሱ የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ በዘርፉ ያሉ ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ሀገራት መካከል አንዷ ለማድረግ ውጥን ይዟል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እንደገለጹት፣ ለውጡን ተከትሎ ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎችና አዳዲስ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ተግባሩ በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠር አመርቂ ውጤት እዲመዘገብ ማስቻሉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ፣ በበጀት ዓመቱ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
አዲሱን የቱሪዝም ፖሊሲ በመተግበር የቱሪዝም ዕድገቱን ይበልጥ ማስቀጠል የበጀት ዓመቱ ዋነኛው እቅድ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት ተጠናቆ ለሚመለከተው አካል እንዲጸድቅ መላኩንም አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ አብዛኞቹ የቱሪስት መዳረሻዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑም ነው አቶ ስለሺ የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት በላሊበላ፣ በጣና ገዳማት ደጋ እስጢፋኖስ፣ በባሌ ተራራ ብሄራዊ ፓርክ እና በድሬዳዋ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቱሪስት መረጃ ማዕከል ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በአብዛኞቹ ክልሎች ሰፋፊ የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ ጠንካራና የተደራጀ የማስተዋወቅ እና የገጽታ ግንባታ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ተናግረዋል።