ቀጥታ፡

በዓለም ላይ የኢትዮጵያን ተቀባይነት በይበልጥ የሚያሳድጉት ፕሮጀክቶች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ያስመረቀቻቸው፣ የጀመረቻቸው እና በቀጣይ ለመጀመር የወጠነቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ከአኅጉር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ያሳድጋሉ።

በቅርቡ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ያሉ እና የምትገነባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ትሩፋት ከሀገር አልፎ ለጎረቤት ጭምር መሆኑን የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ውስብስብ ሂደቶችን በመሻገር ዕውን ያደረገችው የሕዳሴ ግድብ ከእንግዲህ በኋላ የሚያቆማት እንቅፋት እንደሌለ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህ ስኬት ኢትዮጵያውያ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደሚችሉ ማነሳሳትን ያጎለበተ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የጋዝ፣ ነዳጅ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች፣ የኒውክሌር ፕላንቴሽንና ሌሎችም ሜጋ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በኢነርጂ ብቻ ሳይሆን በብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች በረከቶችን ለአፍሪካ ብልጽግና እየተጋች መሆኗን የሚገልጹ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጉዞ ላይ ነች፤ ከዚህ ጉዞዋ የሚያናጥባት እንደሌለም የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ረትታ በነጻነት ፖሊሲ እየነደፈች ብሎም እየተገበረች የይቻላል መንፈስንም እያሰረጸች መሆኗ ምስክር መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ስትበለጽግ ቅድሚያ ሕዝቧ ከዚያም ጎረቤቶቿ ተጠቃሚ መሆናቸውን አጢነው፤ በዚህ አግባብ በይበልጥ ለኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት በአንድነት መቆም እንደሚመከርም አስገንዝበዋል።

የሜጋ ፕሮጀክቶች መብዛት በዓለማቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ የመፍጠር ዐቅምን እንደሚያሳድግ ጠቁመው፤ ድህነትን በመቅረፍ የጎላ አስተዋጽኦ በማድረግ በቀጣናው ብሎም በዓለም መድረክ በልበሙሉነት ሁኔታዎችን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገርን ገጽታ ከፍ ማድረጉን ገልጸው፤ የተጀመሩ እና በቀጣይ የሚሠሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችም ኢትዮጵያን የመረዳት ዕይታን ያጎለብታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ከፍታና የማድረግ ብቃት በማሳለጥ ተቀባይነቷን ይበልጥ እንደሚያሳድገው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም