የክህሎቶች ልማት፤ የአፍሪካ ቀጣይ የእድገት ምዕራፍ እና ግንባር - ኢዜአ አማርኛ
የክህሎቶች ልማት፤ የአፍሪካ ቀጣይ የእድገት ምዕራፍ እና ግንባር

አፍሪካ የተስፋ እና የበረከት አህጉር ብቻ አይደለችም የዓለም ቀጣይ የእድገት ዳርቻ እና ማዕከል ጭምር እንጂ። ህዝቧ እ.አ.አ በ2024 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ተሻግሯል፤ እ.አ.አ በ2050 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል። ከአንድ ትውልድ በኋላ ባለንባት ምድር ላይ ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ ከአፍሪካ እንደሚሆን ይጠበቃል። በጣም አስገራሚው ነገር ከ60 በመቶ በላይ አፍሪካውያን እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ሲሆን ይህም አፍሪካን ወጣቷ አህጉር አድርጓታል።
ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ወጣት ትልቅ የስነ ህዝብ ትሩፋት ነው። ይህን አቅም ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ከተቻለ አፍሪካን የዓለም ክህሎት መፍለቂያ፣ የፈጠራ እና ኢኖቬሽን ማዕከል ማድረግ ይቻላል።
ይሁንና የስነ ህዝብ ትሩፋት ብቻውን ልማት እንዲረጋገጥ አያስችልም። እውነተኛው ፈተና ያለው ይህን የተትረፈረፈ የሰው ሀብት በክህሎት የዳበረ፣ ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ራሱን ብቁ ያደረገ እና መፍጠር ወደ ሚችል የስራ ኃይል መቀየር ላይ ነው።
የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 የሰው ኃይል “የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመፍጠር” የሚያስችል ዋንኛ ምሰሶ እንደሆነ ያስቀምጣል። ይህ አህጉራዊ ማዕቀፍ በእውቀት እና ሁሉን አቀፍ እድገት አማካኝነት የበለጸገች፣ የተሳሰረች እና ራሷን የቻለች አህጉርን የመፍጠር ራዕይን አንግቧል።
አፍሪካ የሰው ሀብት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሀብቶች ባለጸጋም ናት። አፍሪካ የዓለማችን 30 በመቶ የማዕድን ሀብት የሚገኝባት አህጉር ናት። ኮባልት፣ ሊቲየም፣ ፕላቲኒየም እና ሌሎች ውድ ማዕድናትን በስፋት ይገኙበታል። ማዕድናቱ አሁን ዓለም ላለችበት አረንጓዴ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ቁልፍ የሚባሉ ናቸው።
የዓለማችን 60 በመቶ ያልታረሰ መሬት ያለው በዚችሁ አህጉር ነው። ይህ እርሻ የማያውቀው መሬት የዓለምን የምግብ ስርዓት በከፍተኛ ሁኔታ የመቀየር አቅም አለው። ከ10 ቴራ ዋት በላይ የፀሐይ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላት አፍሪካ ከአህጉር አልፋ የኢንዱስትሪ እና ዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በኃይል የማመንበሽበሽ አቅም አለው።
የኢኮኖሚ ማዕበሉም ወደ አፍሪካ ያደላ ይመስላል። እ.አ.አ 2021 ገቢራዊ መሆን የጀመረው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና 55 ሀገራትን የሚያስተሳስር እና 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ተጠቃሚን በአንድ ማዕቀፍ ስር የሚያሳባስብ ነው። በአህጉር ደረጃ ዓመታዊ ጥቅል ምርቱ (ጂዲፒ) 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ይገመታል።
አህጉራዊ የንግድ ማዕቀፉ በሙሉ አቅሙ ሲተገበር የአፍሪካ ሀገራትን የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ መጠን 50 በመቶ እንደሚጨምረው የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል። ይህም ለአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማትን የሚያፋጥንና አህጉሪቷ ጥሬ እቃዎችን ወደ ውጭ ልካ መልሳ ያለቀላቸውን ምርቶች በከፍተኛ ወጪ ከመግዛት ተላቃ ጥሬ ምርቶቿን በከፍተኛ ጥራት ወደ ማምረት ያሸጋግራታል። ይህ ትልቅ የኢኮኖሚ ትስስር እድል አፍሪካውያን በጋራ እንዲለሙ፣ የሙያ ክህሎት እንዲያሳድጉ እና የእውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ እንዲሁም ጠንካራ እና የማይበገር ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶች እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል።
እነዚህ ሁላ ተስፋ ሰጪ አቅሞች የሚቃረን አንድ የማይካድ ሐቅ አፍሪካ ውስጥ አለ ይህ እውነት የአፍሪካን የእድገት አቅም በሚፈለገው መልኩ የሚመግብ የክህሎቶች እና የስራ ክፍተት ነው። በየዓመቱ በአፍሪካ ከ10 እስከ 12 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች ወደ ስራ ይገባሉ። ይሁንና በአህጉሪቷ በዓመቱ የሚፈጠረው መደበኛ ስራ 3 ሚሊዮን ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ከሆነ ከአፍሪካ ወጣቶች መካከል አንድ ሶስተኛ ገደማው ስራ አጥ (Unemployment) ወይም ከአቅም በታች ሰራተኝነት (Underemployment) ውስጥ ነው። ይህ ስራ አለማግኘት ያለው በአፍሪካ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢነርጂ፣ ቴክኖሎጂ፣ በዲጂታላይዜሽን እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚገኙ ኩባንያዎች ክህሎት ያለው ሰው አጠረን እያሉበት ባሉበት ወቅት መሆኑ ትልቅ ጥያቄን ያስነሳል። በትምህርት ስርዓቱ እና በገበያው ፍላጎት መካከል እንዴት እንደዚህ አይነት አለመጣጣም ሊመጣ ቻለ? የሚል። በትምህርት እና በኢንዱስትሪው መካከል ባለው ያለመተሳሰር ችግር ምክንያት አፍሪካ በየዓመቱ 130 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ምርታማነት (productivity) ታጣላች።
እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ጉዳይ ፈተናው የአቅም ሳይሆን ትምህርት እና ስራን፣ ፖሊሲ እና ተግባርን እና ስልጠናን ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያስተሳሰር መስመር አለመዘርጋቱ ነው። በአፍሪካ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት እየሰሩ ያሉት ከኢንዱስትሪው ርቀው ነው ማለት ይቻላል ይህም ተመራቂዎች የስራ ገበያው የሚፈልገውን ክህሎት እና አቅም እንዳይታጠቁ አድርጓል። ሌላኛው ፈተና በአፍሪካ የተንሰራፋው ኢ-መደበኛ ኢኮኖሚ ነው። አንዳንድ ጥናቶች የአፍሪካን ኢ-መደበኛ የኢኮኖሚ ድርሻ እስከ 85 በመቶ ያደርሱታል። ይህም ዜጎች ክህሎታቸውን እንዳያሳድጉ እና የብቃት ማረጋገጫን እንዳያገኙ እክል ፈጥሯል።
የአፍሪካን ክህሎት ምህዳር በመቀየር የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የስራ እድል ፈጠራን ማሳደግ እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ላይ የጋራ ትብብርን ማጠናከር አበይት ትኩረቱ ያደረገ ሁለተኛው የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
“አፍሪካውያንን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማት የሚያፋጥኑበትን ክህሎቶች ማስታጠቅ” የሳምንቱ መሪ ሀሳብ ነው።
ሁነቱን ያዘጋጁት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው።
በሁነቱ መክፈቻ ላይ በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ እና የህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች እና የአባል ሀገራት ሚኒስትሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች፣ የልማት ተቋማት አመራሮች፣ መምህራን፣ ኢኖቬተሮች፣ የወጣት ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ተሳትፈውበታል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ክህሎቶች ለሀገራዊ ግቦችና ለአህጉራዊ የ2063 የልማት አጀንዳዎች መሳካት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ናቸው።
ኢትዮጵያ ለክህሎት ልማት በሰጠችው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው ብለዋል።
ክህሎት መር የፖሊሲ እርምጃችን ወጣቶች ከስራ ፈላጊነት ወደ ስራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ የስራ ፈጣሪነት ባህልን በንቃት እያስተዋወቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ተመራቂዎች የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ እና እድገት እንዲያመጡ የሚያስፈልጋቸውን ስልጠና፣ ምክር እና የገንዘብ ድጋፍ እያመቻቸ መሆኑን አመላክተዋል።
በስልጠና ተቋማት እና በኢንዱስትሪዎች መካከል ያለውን ትብብር የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው የህዝባችንን አቅም ወደ ውጤታማ፣ አሳታፊ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወደሆነ የሥራ ኃይል መለወጥ አለብን ብለዋል።
ክህሎት የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል።
የክህሎት ልማት ለአሳታፊ ዕድገትና ለተገቢ የሥራ ዕድሎች ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የትግበራ ዕቅድ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
አባል ሀገራት ሀገራዊ ለውጦችን ከአህጉራዊ ፍላጎቶች ጋር ለማጣጣም በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የተሻለ፣ ፈጣን እና ይበልጥ አሳታፊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያለውን የለውጥ አቅም መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል። የፖሊሲ ወጥነትን እና ቀጠናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ክህሎት ክፍተትን መሙላት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ለክህሎት ልማት መጠቀም እና በአጀንዳ 2063 አማካኝነት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ ላይ ውይይት ይደረጋል።
በሳምንቱ የሚኒስትሮች እና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮች፣ የክህሎት አውደ ርዕዮች እና የገበያ ትስስር ሁነቶች እንዲሁም የወጣቶች እና የስራ ፈጣሪዎች ፎረም እንደሚካሄድ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል። ፎረሙ የአፍሪካ ኢኖቬተሮች የስራ ውጤቶች ይቀርቡበታል።
የክህሎቶች ሳምንት ተሳታፊዎቹ በኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት እና በኢኖሼሽን ማዕከላት ውስጥ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው የሚገኙ የሰው ኃይል ልማት ስራዎች ይጎበኛሉ።
ሳምንቱ እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የአፍሪካ ክህሎት ልማት አስመልክቶ የጋራ አቋም መገለጫ እና የድርጊት መርሃ ግብር ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት ለአህጉሪቷ የኢንዱስትሪ እና ክህሎት አጀንዳ ተጨባጭ አሻራ የሚያሳርፍ መሆኑን ህብረቱ ገልጿል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት እ.አ.አ ኦክቶበር 2024 በጋና አክራ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
የአፍሪካ ክህሎቶች ፈተናዎች ክፍተቶች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ እንዲሁም ምህዳሩን ለመቀየር አህጉሪቷ በዘርፉ አብዮት ያስፈልጋታል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህን የስነ ህዝብ ትሩፋት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ክህሎት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል መቀየር ይገባል።
ይህን ለማድረግ የተቀናጀ እና አህጉር አቀፍ ጥረት ያስፈልጋል።
የሁለተኛው የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት ስኬት የሚለካው በንግግሮች እና በጋራ መግለጫዎች ሳይሆን ራዕዮቹን በአፍሪካ ትምህርት ተቋማት፣ ስልጠና ማዕከላት እና ኢንዱስትሪዎች በተጨባጭ በመቀየር እና ውጤት በማምጣት ነው።
በዚህ ረገድም መንግስታት፣ የትምህርት ተቋማት፣ ኢንዱስትሪዎች እና ወጣት ስራ ፈጣሪዎች የአፍሪካን የክህሎት ልማት መጻኢ ጊዜ በውድድር፣ በፈጠራ እና አሳታፊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊገነቡ ይገባል።
አፍሪካ ወጣቶቿ በክህሎት እና በእውቀት ከታጠቁ አፍሪካ የተለመቻቸውን ግዙፍ እቅዶች እና ትላልቅ ውጥኖች ባጠረ ጊዜ እንዲሳኩ ያስችላል።