ቀጥታ፡

የሰላም ጉዳይ የጋራ በመሆኑ በዘላቂነት ማፅናት የጋራ ስራችን ሆኖ ይቀጥላል - የኃይማኖት አባቶች

ወልዲያ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ የሰላም ጉዳይ የጋራ ህልውና ጉዳይ በመሆኑ በዘላቂነት ማፅናት የጋራ ስራችን ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ የወልዲያ ከተማ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

በወልዲያ ከተማ የተለያዩ ኃይማኖቶች መሪዎችና አባቶች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች በተገኙበት "ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ በሰላም ጉዳይ ላይ ዛሬ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።


 

የኃይማኖት አባቶቹ በሰላም ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም ይዘው እንደሚሰሩ በመድረኩ አረጋግጠዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሸሕ ሃሰን የሱፍ፣ መምሕር ደስታው አስናቀ እና መምሕር ዘማርያም አማረ፤ የሰላም ማጣት ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ የሰላም ጉዳይ ለማንም የማንተወው የጋራ ጉዳያችን ነው ብለዋል።

በሁሉም ቤተ እምነቶች በሀገር ሰላምና አንድነት እንዲሁም በሰው ልጆች ዘንድ ሰላምና ፍቅርን መስበክ የግድ መሆኑን አንስተው፤ እኛም በዚሁ መንገድ እንቀጥላልን ነው ያሉት።

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ፤ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላም ባላቸው ቀናኢነት የከተማዋ ሰላም ተጠብቆ መዝለቁን ተናግረዋል።

በመሆኑም ሰላምን በዘላቂነት በማፅናት ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ይሄው ጠንካራ አቋም ጎልብቶ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በመከላከያ ሰራዊት የ11ኛ ዕዝ ዋና አዛዠ ሜጀር ጀኔራል አድማሱ ዓለሙ፤ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የታሪካዊ ጠላቶቻችንና የባንዳዎች የጥፋት ሴራን በማክሸፍ የሀገሩን ክብርና ሉአላዊነትና የሕዝብን ሰላም በአስተማማኝ መልኩ እያስጠበቀ መሆኑን አንስተዋል።

በዚሕ ረገድ የሕዝቡ ጠንካራ ድጋፍና ትብብር እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ሰላምና ፍቅርን በማስተማር እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው፤ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው በበኩላቸው፤ ከሕዝብ አብራክ የወጣው መከላከያ ሰራዊት ከምንም በላይ ሀገሩንና ሕዝቡን አስቀድሞ ሌት ተቀን ዘብ ሆኖ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚሕም የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት እንዲሁም የሕዝቦቿ ደሕንነት በአስተማማኝ መልኩ ተጠብቆ እየዘለቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሕ ረገድ ሕዝቡ ለሰራዊቱ ያለው ድጋፍ፣ ፍቅርና አብሮነት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ ለሀገር ሰላምና ደሕንነት የሕዝቡ ትብብርና አጋርነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ሰራዊቱ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም፣ ክብርና ሉአላዊነት እንዲሁም የሕዝብን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም