ቀጥታ፡

የማር ጥራት ፍተሻን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማካሄድ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦የማር ምርትን የጥራት ፍተሻ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማካሄድ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት አስታወቀ።          

ድርጅቱ ፍተሻውን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ አቅም ለማካሄድ ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽነት መርሃ ግብር ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።   


 

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የማር ምርት አቅም ቢኖርም በሚፈለገው ልክ የውጭ ምንዛሬ እየተገኘበት አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የማር ጥራት ጉዳይ አንዱና ዋነኛው ነው ተብሏል።  

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የፍተሻ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ምትኩ ድሪባ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የማር ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የጸረ ተባይ ቅሪት ፍተሻ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ አቅም ለማካሄድ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው።  


 

ለዚህም ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለፍተሻ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ዝግጁ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

ፍተሻውን ለማከናወን ክህሎት ያለው ባለሙያ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ከውጭ በመጣ አሰልጣኝ ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።    

ከዚህ ቀደም በማር ላይ የሚገኘውን የጸረ ተባይ ቅሪት ፍተሻ የሚደረገው ናሙና ወደ ውጭ ተልኮ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ፍተሻውን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል። 


 

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን ጠቁመው፤ ተወዳዳሪ ለመሆን መሰል የላብራቶሪ አቅም መገንባቱ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።  

የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድም ፍተሻው  በሀገር ውስጥ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል። 

በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የምግብና መጠጥ ፍተሻ ላቦራቶሪ ሲኒየር አናሌቲካል ኬሚስት ብሩክ ስለሺ በበኩላቸው፤ የአቅም ግንባታ ስልጠናው በሌሎች ምርቶች ላይም የጸረ ተባይ ቅሪትን መፈተሽ የሚያስችል አቅም ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።  


 

በተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽነት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን መንገሻ በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የላቦራቶሪ አቅም እንዲገነባ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።    


 

ለላቦራቶሪ የሚያስፈልጉ የተለያዩ መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች የሥራ ላይ ስልጠና እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለማር ምርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ተደራሽ መደረጋቸውን የገለጹት አስተባባሪው፤ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ልምድ ተቀምሮ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም