ቀጥታ፡

በዞኑ ጠንካራ የፍትህ ተቋማትን በመገንባት የህግ የበላይነትን  ለማረጋገጥ  ትኩረት ተሰጥቷል

ገንዳውሃ ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን ጠንካራ የፍትህ ተቋማትን  በመገንባት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሰላምን ማፅናት  የሚያስችሉ ተግባራት  በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ። 

በዞኑ የከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ዛሬ በገንዳውሃ  ከተማ ተካሂዷል። 


 

በመድረኩ ላይ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ኢብራሂም የሱፍ እንዳመለከቱት፤ ወንጀልን ለመከላከል የፍትሕ ተቋማት መጠናከር አለባቸው።


 

የፖሊስ፣ የፍትሕ፣ የፍርድ ቤትና የማረሚያ ቤት ተቋማት ጥምረትና ትብብር ፈጣን፣ ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው የፍትሕ ስርዓት ለመገንባት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። 

የዛሬው መድረክ   ዓላማም ተቋማቱ በቅንጅት በመስራት ሃብትን፣ ጊዜንና የሰው ሃይልን የሚቆጥብ አሰራር በመከተል ሕብረተሰቡ በፍትሕ ላይ ያለውን እርካታ ይበልጥ  ለማሳደግ  ምቹ መደላደልን ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ ቢተው አሳዬ በበኩላቸው፤ ማሕበረሰቡ ሰላምን በመጠበቅ፣ ለሕግ አስከባሪዎች ተባባሪ በመሆንና ጥፋተኞችን በማጋለጥ አስተማማኝ ፍትሕ ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ተሳታፊነቱን ይበልጥ ማጠናከር  እንዳለበት አመልክተዋል። 


 

የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላምን ለማፅናት በሚደረገው ጥረት የፍትሕ ተቋማት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። 

በዞኑ የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው ካለው የፀጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ  የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር ምስጋናው ካሴ ናቸው። 


 

በተለይም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣  የመንገድ ላይ ዝርፊያና እገታን ለመቆጣጠር  ሕብረተሰቡን  ባሳተፈ መንገድ  እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዞኑ ጠንካራ የፍትሕ ተቋም በመገንባት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሰላምን ማፅናት  የሚያስችሉ ተግባራት  በተቀናጀ አግባብ በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የዘርፉ አመራሮችና  ባለሙያዎች  ገልጸዋል። 

በመድረኩ ላይ ከፖሊስ፣ ፍትሕ፣ ፍርድ ቤትና ማረሚያ ቤት  የተውጣጡ አመራሮች ፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም