ቀጥታ፡

የሰላም ሠራዊት አባላት የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦የሰላም ሠራዊት አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ። 

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የመስቀል ደመራ፣ የኢሬቻ በዓላትና የተለያዩ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሰላም ሠራዊት አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሐ ግብር አካሄዷል።  


 

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት፤ በ2018 ዓ.ም የተከበሩ ሃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት እንዲሁም የተለያዩ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የሰላም ሠራዊቱ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። 

ሕዝቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን ከማድረግ አኳያም ነዋሪው ከሚኖርበት ብሎክ አንስቶ በተለያዩ የሰላምና የፀጥታ አደረጃጀት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። 

በዚህም ሕብረተሰቡ ለከተማዋ ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመልክተዋል። 

የሰላም ሠራዊት አባላት ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

በቀጣይም የሚከበሩ በዓላትና የሚከናወኑ ኹነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፤ የሰላም ሠራዊት ከፀጥታ አካላት ጋር ይበልጥ በመቀናጀት የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ስራዎችን ማጠናከር እንዳለባችው  ጠቁመዋል። 

የሰላም ሠራዊቱ አባላትም በቀጣይ ያሉ ኹነቶች ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም