መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና ፍትሃዊ አሰራርን ለመዘርጋት ያስችላል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና ፍትሃዊ አሰራርን ለመዘርጋት ያስችላል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 12/ 2018 (ኢዜአ) ፡- መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትን በማስቀረት ለዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመዘርጋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
በጋምቤላ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተጀምሯል።
በዚህ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የታቀደውን ልማትና እድገት በማፋጠን ለሕዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
የተቋማትን አገልግሎት በአንድ ቦታ መስጠት የሚያስችለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ደግሞ እንግልትን በማስቀረት ለዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመዘርጋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አንስተው፤ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በማስቀረት ረገድም የጎላ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ለስኬታማነቱ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር የታዩትን የልማት ስኬቶች ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰው ተኮር የአገልግሎት ልህቀታችንን ልናጎለብት ይገባል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕድሴ ግድብ ግንባታ፣ የቱሪዝም መስህብ ማዕከላት ፣የከተሞች ኮሪደር ልማት፣ የሌማት ትሩፋትና ሌሎች የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያ የማንሰራራት መገለጫ መሆናቸውን አንስተዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ መሰረታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ሰው ተኮር የአገልግሎት ልህቀትን በመተግብር ለዜጎች ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል ብለዋል።
በመሆኑም እንደ ሀገር የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ማዘመን ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በክልሉ ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት የማዘመኑ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ላክዴር ላክባክ ናቸው።
በክልል ደረጃ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በጋምቤላ ከተማ አስተዳደርና በዞን መዋቅሮችም የማስፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።