ኢኖቬሽንን የአፍሪካ ልማት ምሰሶ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ገቢራዊ እየሆኑ ነው- የአፍሪካ ህብረት - ኢዜአ አማርኛ
ኢኖቬሽንን የአፍሪካ ልማት ምሰሶ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ገቢራዊ እየሆኑ ነው- የአፍሪካ ህብረት

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ኢኖቬሽን ለአፍሪካ አካታች እና ዘላቂ ልማት አቀጣጣይ ሞተር ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የአፍሪካ ህብረት የኢኖቬሽን ፌስቲቫል በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
“የአፍሪካ ህብረት ወጣቶችን የአህጉራዊ ኢኖቬሽን መሪ የማድረግ ተግባር” የፌስቲቫሉ መሪ ሀሳብ ነው።
በፌስቲቫሉ ላይ ኢኖቬተሮች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የግሉ ዘርፍ መሪዎች እና የወጣቶች ተወካዮች ይሳተፋሉ።
ሁነቱ ለሀገር በቀል የኢኖቬሽን መፍትሄዎች እውቅና በመስጠት ስራዎችን የበለጠ ማላቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
የአፍሪካ ብሩህ አዕምሮዎችን ከፋይናንስ አቅርቦት፣ ዘመኑ ከደረሰበት ክህሎት እና እድሎች ጋር በማገናኘት የኢኖቬሽን ስራዎችን የማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑም ተመላክቷል።
የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቷ ዜጎች የበለጸጉ የኢኖቬሽን መፍትሄዎች ድጋፍ በማድረግ እና ለወጣት መር የኢኖቬሽን ስራዎች ምቹ ምህዳር ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በህብረቱ የዲጂታል እና ኢኖቬሽን ፕሮግራም አማካኝነት ከ10 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 18 ወጣት ኢኖቬተሮችን በተቋሙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች በማሰማራት ለኦፕሬሽን ፈተናዎች የተጠኑ የዲጂታል መፍትሄዎችን እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ፕሮግራሙን የሚደግፍ የአፍሪካ ህብረት የኦኖቬሽን ቤተ ሙከራ በማቋቋም ተቋማዊ የኢኖቬሽን አቅም ለመገንባት እና ትብብርን ለማጠናከር እየተጠቀመ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው።
በዜጎች የቴክኖሎጂ ፈንድ አማካኝነትም 15 ኢኖቬተሮች ዜጎች በፖሊሲ ቀረጻ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያሳድጉ መፍትሄዎችን እንዲያቀርቡ የፋይናንስ እና ቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት እድሜያቸው ከ15 እስከ 25 የሆኑ ወጣት ሴት ኢኖቬተሮች በአህጉሪቷ ያሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዲጂታል እና ቴክኖሎጂ አማራጮች እንዲፈቱ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት ኢኒሼቲቭ ገቢራዊ እያደረገ ነው።
ይህም የስርዓተ ጾታ አካታችነት መሰረት ያደረገ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን እንዲድጉ የሚያስችል መሆኑን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ህብረቱ ኢኖቬሽን የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት እና ሁሉን አካታችና ዘላቂ ልማት የማረጋገጥ ራዕይ አቀጣጣይ እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
የኢኖቬሽን ፌስቲቫሉ እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።