በሚቀጥሉት አስር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ያገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2018 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አስር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ቀደም ብሎ የክረምት ወቅት ዝናብ ሲያገኙ በነበሩት የምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት ያለው ዝናብ ይኖራል።
በሌላ በኩል በሰሜን ምዕራብ እና በሰሜን የሀገሪቱ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል።
የክረምት ወቅት ዝናብ እያገኙ የነበሩት የምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው ርጥበት ለግብርና እንቅስቃሴ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ገልጿል።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት አካባቢዎች የሚጠበቀው ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ርጥበት በወቅቱ ለሚጀመር የግብርና ስራ ከፍተኛ ጠቃሜታ ይኖረዋል ብሏል።
አብዛኛው የበጋ ርጥበት ተጠቃሚ ተፋሰሶች እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን የተቀሩት ተፋሰሶች ዝቅተኛ ርጥበት እንደሚያገኙ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች ያሳያሉ።
ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ፣ ጊቤ፣ መካከለኛውና ታችኛው ስምጥ ሸለቆ፣ ላይኛውና መካከለኛው ገናሌ ዳዋ፣ ላይኛውና መካከለኛ ዋቢ ሸበሌ፣ ታችኛው ኦጋዴን፣ ታችኛው ዓባይ እና ታችኛው ተከዜ መካከለኛ ርጥበት እንደሚያገኙ በመግለጫው ተጠቅሷል።