ኢሬቻ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ማንሰራራት! - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ማንሰራራት!

ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው፤ ሰዎች በክረምት ወቅት ከሚከሰት መለያየትና መራራቅ በኋላ ዳግም የሚገናኙበት፣ በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት ዕለት ነው።
ስለ ሰላምና አንድነት የሚዘመርበት፣ ስለመጪው ጊዜ መልካም ምኞት የሚገለጥበት፣ ሁሉን ላደረገ ፈጣሪ ምስጋና የሚቸርበት የአብሮነት በዓል ነው።
ኢሬቻ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት የሚገለጽበት የገዳ ስርዓት አንዱ አካል ነው፡፡ የኢሬቻ እሴቶች ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላት ሀገር ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው። አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ አብሮነት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ዕርቅ እና ሌሎችም ተጠቃሽ የመልካም እሴቶች መገለጫ ነው።
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የገዳ ስርዓት አንዱ እሴት ኢሬቻ ሲሆን፤ ለሀገር ማንሠራራትና ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ መሠረት ይሆናል፡፡
ኢሬቻ አብሮነት የሚጸናበት፣ የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት ይበልጥ የሚጎላበት፣ አሰባሳቢ ትርክት የሚጎለብትበት፣ ሁሉም በጋራ የሚያከብረው የፍቅር፣ የአንድነት እና የአብሮነት ማሰሪያ ከፍ ያለ በዓል ነው፡፡
ኢሬቻ በጋራ የሚያከብሩትና የዓለም ቱሪስቶች የሚታደሙበት ሲሆን፤ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የኢትዮጵያ ድንቅ ባህል ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡
የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል አከባበር ሀገራዊ ማንሰራራት በተግባር የተረጋገጠበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተመርቆ ዓለም የኢትዮጵያን መቻል በተግባር ባየበትና ሌሎች ለሀገር ማንሰራራት ዕውን መሆን መሠረት የሚጥሉ ትላልቅ ሀገራዊ ኘሮጀክቶች ይፋ በተደረጉበት ማግስት መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡
በዓሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመላው ኢትዮጵያዊያንን ሕብረት የሚንጸባረቅበት ሆኖ በተለያዩ አከባቢዎች በድምቀት እየተከበረም ይገኛል፡፡
በልመናው፣ በምርቃቱ፣ በምስጋናው ሁሉ ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን! አሜን! አሜን!) የሚሉ ድምፆች ይስተጋባሉ።
Hayyee! Hayyee! Hayyee!
Hayyee! Hayyee! Hayyee!
Waaqa Uumaa, Waaqa Uumamaa ፍጥረትን የፈጠርክ ፈጣሪ
Gurraacha garaa garbaa የእውነትና የሰላም አምላክ!
Dogoggora nu oolchi ከስህተትና ከክፉ ነገሮች ሁሉ ጠብቀን!
Dacheef nagaa kenni ለምድራችን ሰላም ስጥ!
Laggeenif nagaa kenni ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!
Olota keenyaaf nagaa kenni ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!
.
.
. Loowan keenyaaf nagaa kenni " ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!" በማለት ይመረቃል።
ሕዝቡም ይሁንልን ይደረግልን ሲል "አሜን! አሜን! አሜን!” ይላል።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም በማግስቱ እሑድ መስከረም 25 ቀን በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዲ " ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት " በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል።
የክራምት ወራት እንዳበቃ የሚከበረው "ኢሬቻ መልካ" Irreecha Birraa (በውኃ ዳርቻ የሚከበር) ሲሆን፤ በዓመቱ አጋማሽ ላይ "ኢሬቻ ቱሉ" Irreecha Arfaasaa ደግሞ በተራራማ ቦታ ይከበራል።
ኢሬቻ መልካ የሚከበረው በመስከረም ወር ከመስቀል በዓል በኋላ ነው። የክረምት ወራት የዝናብ፣ የደመና፣ የጭቃና የረግረግ ወቅት አልፎ ለፈካው ወራት በመምጣቱ ምስጋና የሚቀርብበት ነው።
ይህ ከማህበራዊ መስተጋብር አኳያም ሰዎች የሚሰባሰቡበትና የሚገናኙበት ነው። ከባዱ የክረምት ወቅት አልፎ ብርሃን (ብራ) ስለደረሰ ለዚያ ምልክት ይሆን ዘንድ የለመለመ እርጥብ ሣር ይዘው ወደ ወንዝ በመውረድ ንጹህ ውሃ ውስጥ እየነከሩና እየረጩ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው፡፡
ኢሬቻ ቱሉ የሚከበረው የበጋው ወራት አልፎ የበልግ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ነው። በዚህም ፈጣሪ ''እርጥበት አትንፈገን፣ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይምጡ፤ የዝናብ ንፋስ ስጠን'' በማለት ለፈጣሪ ተማጽኖ የሚቀርብበት ነው።
"ይህን ተራራ የፈጠርክ ፈጣሪ ወቅቱን የሰላም አድርግልን፣ የሰላም ዝናብ አዝንብልን፣ ጎርፍን ያዝልን፣ የተዘራው ፍሬ እንዲያፈራ እንለምንሃለን" እያለ በኢሬቻ ቱሉ ላይ ፈጣሪውን ይለምናል፡፡
በኢሬቻ በዓል የፈጣሪ ምህረት፣ ዕርቅ፣ አብሮነት እና በዓሉ የሰላም በዓል እንዲሆን ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ኦሮሞ ፈጣሪውን ይጠይቃል፤ ይማፀናል፤ ለተደረገለትም ነገር ሁሉ ያመሰግናል።
ኢሬቻ ምድርን እና ሰማይን ለፈጠረው "ዋቃ" "Waaqa" ምስጋናውን ለማድረስ የሚከበር ሲሆን፤ በዕድሜ ልዩነት ሳይገደብ ለዘመናት በጋራ፣ በአንድነትና በፍቅር ሲከበር ቆይቷል።
በዝናባማው የክረምት ወቅት በጅረቶችና ወንዞች መሙላት ምክንያት ተራርቆ የቆየው ዘመድ አዝማድ በኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ሥፍራ ይገናኛል፤ ይጠያየቃል፤ ናፍቆቱንም ይወጣል።
አባቶች ክረምት በለሊት ይመሰላል ይላሉ። ለሊት ደግሞ ጨለማ ነው። ጨለማው ሲነጋ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ብርሃን ደግሞ ውበት ነው፤ መታያና መድመቂያም ነው። ለዚህ ነው በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ሁሉም ውብ የባህል ልብሱን በመልበስ በደስታ በዓሉን ለማክበር የሚመጣው።
ሕዝቡ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ሥፍራ የሚሄደው በተናጠል ሳይሆን በሕብረትና በአንድነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢሬቻ የአንድነትና የአብሮነት በዓል ነው የሚባለው።
ኢሬቻ የወንድማማችነትና የአንድነት አርማ ሲሆን፤ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ፣ የህብረ ብሔራዊ አብሮነት ማስተሳሰሪያም ጭምር ነው፡፡
በኢሬቻ ልዩነት የለም፤ ፀብ የለም፤ ክፋት የለም፤ ይልቁንም ምስጋና ይበዛል፤ ፍቅር ይሰፍናል፤ አብሮነት ያብባል፣ አንድነት ይጸናል።
ኢሬቻ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሰላምና የአብሮነት ምልክት ነው። የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚወጣው ታዳሚም እንደ እርጥብ ሣር ወይም አበባ ያለ እርጥብ ነገር በእጁ ይዞ የበዓሉን ስነ-ስርዓት ያከናውናል።
ይህን የሚያደርገውም "ፈጣሪያችን ሆይ አንተ ያፀደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ ለዚህም እናመሰግንሃለን" በማለት የፈጣሪን መልካምነት ለማሳየት ነው።
በሌላ በኩል እርጥብ ሣር የልምላሜ ምልክት በመሆኑ የመልካም ምኞት መግለጫም ስለሆነም ነው በኢሬቻ በዓል እርጥብ ሣር የሚያዘው።
የኢሬቻ በዓል ሲከበር ከሚከወኑ ሥርዓቶች መካከል ሴቶች ሲቄ፣ እርጥብ ሣር እንዲሁም ጮጮ ይዘው ከፊት ሲመሩ አባ ገዳዎች ደግሞ ቦኩ፣ አለንጌ እና ሌሎችንም በበዓሉ ሥርዓት የሚፈቀዱትን ሁሉ በመያዝ ወደ ሥርዓቱ አከባበር እንዲህ እያሉ ያመራሉ።
ኦ ያ መሬሆ…………………መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ
ያ ዋቃ ኡማ ሁንዳ መሬሆ………………… ያ መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ
ያ ዋቃ ለፋ ኡምቴ መሬሆ………………… ያ መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ
ያ ዋቃ መልካ ኡምቴ መሬሆ………………… ያ መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ እያሉ ያመራሉ።
የሁሉ ፈጣሪ፣ ምድርን የፈጠርክ፣ ወንዙን የፈጠርክ . . . ምስጋና ለአንተ ይሁን በማለት ያመሰግናሉ፤ ይዘምራሉ።
የኢሬቻ በዓል ሥነ-ሥርዓት በአባመልካ ተከፍቶ በአባ ገዳዎች ተመርቆ ከተጀመረ በኋላ መላው ሕዝብ በአንድነት ሥርዓቱን ያከናውናል።
ኢሬቻ ሁሉም በጋራ የሚያከብረው፣ የሁሉም ማጌጫ፣ መድመቂያ እና የአብሮነት መገለጫ ነው።
የበዓሉ ታዳሚዎች ከዋዜማው ጀምሮ በሆረ ፊንፊኔና በሆረ ሀርሰዲ በመሰባሰብ፤ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎችን በማዜምና ምስጋና በማቅረብ አድረው በነጋታው ዋናውን የምስጋና በዓልም ያከናውናሉ፡፡
የበዓሉ ታዳሚዎች የደስታና የምስጋና ምልክት የሆነውን ባህላዊ ነጫጭ ልብስ ለብሰው፣ ባህልን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ሁነቶችን በመከወን ልዩ ልዩ ዜማዎችን በማዜም፣ ግጥሞችን በማቅረብ፣ ወደ ፈጣሪ በመጸለይ እና ምስጋና በማቅረብ ሥርዓቱን ያከናውናሉ፡፡
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች የሚታወቁበትን ባህላዊ ልብስ በመልበስ በቋንቋቸው ፈጣሪን እያመሰገኑ በዓሉን በአንድነት ያከብራሉ።
ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በርካታ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ከማቀራረብና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ከመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋጾኦ ያለው ነው፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ በዓላት ላይ ለመታደም ወደ አገር ቤት ይመጣሉ። የውጭ አገራት ጎብኚዎችና እንግዶችም በትዕይንቱ ይታደማሉ።
ለአብነትም ባሳለፍነው ዓመት ከኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ታንዛኒያ አገር የመጡ ልዑካን በበዓሉ ላይ በመታደም የበዓሉን ትልቅነት እና የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ መሆኑን መመስከራቸው ይታወሳል።
አያሌ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ያሉት ይህ የምስጋና በዓል እውነተኛ ወንድማማችነት የሚታይበት፣ አንድነት የሚጎላበት፣ አብሮነት የሚጠናከርበት፣ ሰላምና ተስፋ የሚታወጅበት አገራዊ እሴት ነው።
በባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ ምግቦችና ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማት ኢሬቻና መሰል የአደባባይ በዓላትን እንደመልካም የገበያ አማራጭ ይጠቀሙባቸዋል።
የኢሬቻ በዓል ለቱሪዝም ፍሰት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው፤ በርካታ የባህር ማዶ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የሚታደሙበት በዓል ነው፡፡
በዓሉ ትልቅ የቱሪዝም መስህብ ሲሆን፤ ዘርፉን በማጠናከር እና ብሔራዊ ልማትን በማሳደግ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚናንም የሚጫወት ነው፡፡
ኢሬቻ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁሶች በስፋት የሚተዋወቁበት ታላቅ መድረክ ነው። በእርግጥም ይህንን ውብ የጋራ እሴት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል።
ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነውና በምስጋና እንደጀመርን በምስጋናና ምርቃት እንሰነባበት።
"ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
ከመጥፎ ነገር ጠብቀን!
ንጹህ ዝናብ አዝንብልን!
ከእርግማን ሁሉ አርቀን!
እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!
ከረሃብ ሰውረን!
ከበሽታ ሰውረን!
ከጦርነት ሰውረን!
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!