ስፖርት
በፕሪሚየር ሊጉ ቀዳሚ ስፍራ ላይ የሚገኙት መቻልና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
Apr 6, 2024 147
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በሊጉ ቀዳሚ ስፍራ ላይ የሚገኙት መቻልና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። የመቻልና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይከናወናል። በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመራ በፕሪሚየር ሊጉ ስኬታማ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው መቻል ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፏል፤ በ39 ነጥብም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው በአንዱ ተሸንፏል። በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ፈረሰኞቹ በ37 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በሌላኛው የ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከሻሸመኔ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ የሚጫዎቱ ይሆናል። በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፎ በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። ባህር ዳር ከተማ በ29 ነጥብ በሊጉ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ሻሸመኔ ከተማ ካለፉት አምስቱ የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በአራቱ ሽንፈት ገጥሞታል። በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ የሚመራው ሻሸመኔ ከተማ በ12 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ በወራጅ ቀጣና ላይ ይገኛል። በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ሃዋሳ ከተማን 3 ለ 2 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከነማን 2 ለ 1 አሸንፈዋል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ40 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል።                    
በሀገር አቀፍ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወደ 37 ሺህ ለማድረስ  እየተሰራ ነው
Apr 5, 2024 172
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወደ 37 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የስፖርት ፖሊሲው መንግስት የዜጎችን አካላዊ እንቅስቃሴና ተሳትፎ ለማጎልበት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲገነቡ፣ እንዲጠበቁና ተደራሽ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስቀምጣል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ልማትና አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አዝመራው ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት ሕብረተሰቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲስፋፋ ጥያቄዎችን እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።   የማዘውተሪያ ስፍራዎች በሚፈለገው መጠን አለመዳረሱ ዜጎች የአስፋልት መንገድና ሌሎች ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በማይሆኑ ስፍራዎች ላይ ለመጫወት ይገደዳሉ ብለዋል። መንግስት የዜጎችን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች 34 ሺህ 694 የነበረ ሲሆን በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ 35 ሺህ 953 ከፍ ማለቱን ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል። በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ የስፖርታዊ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ቁጥር ወደ 37 ሺህ 078 ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በተከለሰው የ2016-2018 የመካከለኛ ዘመን የልማት እና የኢንቨስትመንት ዕቅድ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ወደ 50 ሺህ ለማድረስ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል። መንግስት በመካከለኛ ዘመን የልማትና የኢንቨስትመንት ዕቅድ ማብቂያ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል። መንግስት በአንድ ቀበሌ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ በሚል ሀሳብ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ለማስፋት እየሰራ እንደሚገኝም ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው ያብራሩት። የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በአንድ ቀበሌ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲኖር ውሳኔ ማስተላለፉን ለአብነት ጠቅሰዋል። የሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ጨምሮ ሌሎች ክልሎችም እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲስፋፋ፣ እንዲገነባና እንዲታደስ በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።   ይህም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽነት ከማሳደግ አኳያ ጉልህ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማሰራት እያከናወኑ ያለው ተግባር ለክልሎች፣ ተቋማትና ባለሀብቶች አርአያ ሆኗል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ በመከተል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የመዲናዋ ወረዳዎች አዳዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የመገንባትና ነባሮቹን የማደስ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በትምህርት ቤቶች፣በመኖሪያ አካባቢዎችና ተቋማት የሚከናወኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። መንግስት በቀጣይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ ደረጃቸውንና ጥራታቸውን ተጠብቆ እንዲገነቡ በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል።    
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
Apr 4, 2024 200
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፡የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ። በመርኃ ግብሩ መክፈቻ ወልቂጤ ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ወልቂጤ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም ፣ በሁለቱ ሲሸነፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል። ክለቡ በ12 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ተቀምጧል። በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፣ በሶስቱ ሽንፈት ሲያጋጥመው በሁለቱ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በሌላኛው የ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርኃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል ፣ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። ንግድ ባንክ በ37 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ተጋጣሚው ሀምበሪቾ ዱራሜ በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፣ በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጊዜያዊ አሰልጣኙ ብሩክ ሲሳይ የሚመራው ሀምበሪቾ ዱራሜ በ7 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል። የፕሪሚየር ሊጉ የ20ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ነገ ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ፤ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የሊጉ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ። መቻል በ39 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል። የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌይማን በ11 ግቦች ሲመራ ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ የፊት መስመር ተሰላፊ ቻርልስ ሙሲጌ በ9 ግቦች ይከተላል።    
በ45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ አትሌቶች አቀባበል ተደረገ
Apr 2, 2024 218
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው 45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ አትሌቶች በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ናቸው።   በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና ሌሎችም የፌዴሬሽን አመራሮች በመገኘት ለአትሌቶቹ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው የ45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ምድቦች ማለትም 8ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ወንዶች፣ 6 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ሴቶች፣ 4x2 ኪሎ ሜትር የድብልቅ ሪሌ ሴት/ወንድ፣ የ10 ኪሎ ሜትር የአዋቂ ሴቶች እና አዋቂ ወንዶች በተካተቱበት ውድድር ከ51 ሀገራት 485 የሚሆኑ አትሌቶች ተፎካክረውበታል። በዚህም ውድድር ኢትዮጵያ በ14 ሴት እና በ14 ወንድ በ28 አትሌቶች የተወከለች ሲሆን በሁለት ወርቅ፣ በስድስት ብር እና በሁለት ነሃስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳሊያ ከዓለም የሁለተኛነት ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማመቻቸት ተተኪዎችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል
Mar 30, 2024 391
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 21/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችንና ውድድሮችን በማመቻቸት ተተኪዎችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ስፖርት ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ ገለጹ። መላው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህላዊና ዘመናዊ የስፖርት ውድድር በአርባ ምንጭ ከተማ ተጀምሯል። በውድድሩ መክፈቻ ላይ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊና የስፖርት ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ እንዳሉት፤ ክልሉ እምቅ የስፖርት አቅም ያለበት አካባቢ ነው። ይህንን አቅም በመጠቀም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የማዘውተሪያ ስፍራና ውድድሮችን ማመቻቸት ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው ብለዋል። በየአካባቢው ወጣቱ በውስጡ ያለውን የስፖርት ዕምቅ አቅም አውጥቶ እንዲጠቀም ለማድረግ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ማልማትና ለማጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በየትምህርት ቤቶችና በየዞኖቹ በተለያዩ ዘርፎች ውድድሮች እንዲካሄዱና ስፖርተኞች ራሳቸውን እንዲያበቁና እንዲፈትሹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። ዶክተር አበባየሁ ታደሰ አክለውም የዘንድሮው መላው የክልሉ የዘመናዊና ባህላዊ ስፖርቶች ውድድር ለ12 ቀናት እንደሚቆይ ጠቅሰው፤ የስፖርት ቤተሰቡ ፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት በማሳየት ለዘርፉ ዕድገት የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።   የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አርሻሎ አርካሌ በበኩላቸው፤ በክልሉ ተሰጥኦ ያላቸው ሆኖም ዕድል ያላገኙ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ዕድሎችን በማመቻቸት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ የተጀመረው መላው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውድድር በሁለቱም ጾታ በ15 የውድድር ዘርፎች የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል በውድድሩም ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ስፖርተኞች መገኘታቸውን አመልክተዋል።   የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ መኮንን ታደሰ በበኩላቸው ውድድሩ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ በውድድሩም ወንድማማችነትና እህትማማችነት በማጉላት ግቡን እንዲመታ ተወዳዳሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ መለዕክት አስተላልፈዋል። በመክፈቻው መርሃ-ግብር የጋሞ ዞን ከኮንሶ ዞን ጋር ባደረገው የእግር ኳስ ውድድር የጋሞ ዞን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፏል። ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የስፖርት ቡድኖች የየአካባቢያቸውን ባህል ትርኢት አሳይተዋል።  
የክልሉ ባህላዊና ዘመናዊ የስፖርት ውድድር ፌስቲቫል መካሄድ ጀመረ
Mar 30, 2024 304
አርባ ምንጭ ፤ መጋቢት 21/2016 (ኢዜአ)፡- መላው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህላዊና ዘመናዊ የስፖርት ውድድር ፌስቲቫል በአርባ ምንጭ ከተማ መካሄድ ጀመረ። የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ደለለኝ ሀብታሙ እንደገለጹት፣ ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል። ውድድሩ በ15 ባህላዊና ዘመናዊ የስፖርት አይነቶች እንደሚካሄድም ተናግረዋል። በክልሉ ከሚገኙ 12 ዞኖች የአካባቢያቸውን ባህል የሚያሳዩ ልዑካን ቡድኖች እና ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ለውድድሩ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ መግባታቸውን ተናግረዋል። የውድድሩ ዓላማ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ፌስቲቫል ክልሉን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሆነም አስረድተዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በከፍተኛ ንቅናቄ እየተካሄደ ያለውን የማስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን በማጠናከር ማህበረሰቡን ተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመታደግ ያለመ እንደሆነም ገልጸዋል። ክልሉ ያለውን የስፖርት አቅም በማሳደግ በየዘርፉ የሚደረግ እንቅስቃሴን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፣ ውድድሩ የዚሁ አካል ነው ብለዋል። በመርሃ ግብሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል። በዛሬ የውድድሩ መክፈቻ ሥነስርአት ላይ የጋሞ ዞን ከኮንሶ ዞን ጋር የእግር ኳስ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።  
45ኛው የዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ ይካሄዳል
Mar 30, 2024 198
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦45ኛው የዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዛሬ በሰርቢያ ቤልግሬድ ይደረጋል። በሻምፒዮናው ላይ ከ51 አገራት የተወጣጡ 485 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል። በዚህ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ14 ሴትና በ14 ወንድ በአጠቃላይ በ28 አትሌቶች እንደምትወከል ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።   በሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት አትሌቶችን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ልምምዳቸውን አድርገዋል። አትሌቶቹ በሦስት ዙር ተከፍለው ሰርቢያ ከገቡ በኋላ ትናንት ልምምዳቸውን ማከናወናቸውንና ሁሉም ተወዳዳሪዎች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል። 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶችና ሴቶች፣ ከ20 ዓመት በታች ወንዶች በ8 ኪሎ ሜትር፣ ከ20 በታች ሴቶች በስድስት ኪሎ ሜትርና 4 በ 2 ኪሎ ሜትር የድብልቅ ዱላ ቅብብል (ሴትና ወንድ) በሻምፒዮናው የሚካሄዱ የውድድር አይነቶች ናቸው። 6 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ከቀኑ 7 ሰዓት፣ 8 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ከቀኑ 7 ሰዓት ከ 35፣ 4 በ2 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ዱላ ቅብብል (ሴትና ወንድ) ከቀኑ 8 ሰዓት 15፣ 10 ኪሎ ሜትር የአዋቂ ሴቶች 8 ሰዓት ከ45 እና የ10 ኪ.ሜ. አዋቂ ወንዶች ውድድር ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ይደረጋሉ። በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች ታደለች በቀለ፣ ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር፣ ብርቱካን ወልዴ፣ መሰረት ሲሳይ፣ በቀለች ተኩ እና መብራት ግደይ ይሳተፋሉ። በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች በሪሁ አረጋዊ፣ ጭምዴሳ ደበሌ፣ ቦኪ ድሪባ፣ ጌታቸው ማስረሻ፣ ታደሰ ወርቁ እና ብርሃኑ ፀጉ ይወዳደራሉ። በ6 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመታት ሴቶች ውድድር ማርታ አለማየሁ፣ አሳየች አይቼው፣ ሮቤ ዳዲ፣ ሽቶ ጉሚ፣ የኔዋ ንብረት እና ለምለም ንብረት ኢትዮጵያውን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው። በ 8 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ሰውመሆን አንተነህ፣ አቤል በቀለ፣ ይስማው ድሉ፣አብዲሳ ፈይሳ፣ መዝገቡ ስሜና ጀንበሩ ሲሳይ ይሳተፋሉ። 4 በ 2 ኪሎ ሜትር የድብልቅ ዱላ ቅብብል (ሴትና ወንድ) ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 አገራት ይሳተፋሉ። በዱላ ቅብብሉ ላይ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁለት ወንድና ሴት አትሌቶችን ታሳትፋለች።  
ትውልድ በአካልና በአእምሮ ዳብሮ እንዲያድግ በከተማችን የህጻናት መጫወቻዎችን እና የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያዎችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ላይ እንገኛለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Mar 30, 2024 117
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2016(ኢዜአ)፦ የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ በአካልና በአእምሮ ዳብሮ እንዲያድግ በከተማችን የህጻናት መጫወቻዎችን እና የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያዎችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ላይ እንገኛለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ዛሬ ጠዋት በብስራተ ገብርኤል አካባቢ ለህጻናት እና ወጣቶች የሚሆን የስፖርት ማዘውተሪያ ገንብተን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል። በምርጫ ወቅት ቃል በገባነው መሰረት ባለፉት 2 ዓመት ተኩል 1236 ሜዳዎችን ገንብተን ለወጣቶቻችን ክፍት ያደረግን ሲሆን ትናንሽ የልጆች መጫወቻዎችን ጨምሮ 12ሺሕ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለመገንባት አቅደን እየሰራን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።   ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ በአካልና በአእምሮ ዳብሮ እንዲያድግ በከተማችን የህጻናት መጫወቻዎችን እና የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያዎችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ላይ እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል። ዛሬ ያስመረቅነው የብስራተ ገብርኤል አካባቢ ስፖርት ማዘወተሪያ ማዕከል ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰራ ሲሆን በውስጡም የእግር ኳስ መጫወቻ፣ 3 በ 1 ሜዳ፣ የተመልካች አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ መሆኑንም አስታውቀዋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕን በወጣቶቹ እና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በዛሬው እለት መካሄድ ይጀምራል
Mar 28, 2024 188
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በኋላ በ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ወደ ውድድር ይመለሳል። በመርሃ ግብሩ መሰረትም መቻል ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው በሶስቱ ተሸንፏል። ክለቡ በ36 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። በሁለቱ ሲሸነፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል። ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሌላኛው የ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ያገናኛል። በአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት ገጥሞታል። አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። ቡናማዎቹ በ29 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በውበቱ አባቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። ክለቡ በ30 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታ ነገም ቀጥሎ ሲውል አዳማ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 10 ሰዓት፤ ሀዲያ ሆሳዕና ከሀምበሪቾ ዱራሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉ 19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ37 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል። የሀዋሳ ከተማው አሊ ሱሌይማን በ10 ግቦች የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ የግብ አስቆጣሪነት እየመራ ነው።
ኢትዮጵያ በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስፖርተኞች ባስመዘገቡት አኩሪ ውጤት ኮርታባቸዋለች
Mar 26, 2024 256
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስፖርተኞች ፈታኙን ሞቃታማ የአየር ንብረት በመቋቋም ባስመዘገቡት አመርቂ ውጤት ኢትዮጵያ ኮርታባቸዋለች ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ። በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስምንተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል። ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ በሚኒስቴሩ የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል። ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በጋና የተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ9 የወርቅ፣ 8 የብር፣ 5 የነሐስ በአጠቃላይ 22 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሁሉም የስፖርት አይነቶች ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ስፖርተኞቹ በጋና የነበረውን ሞቃታማ አየር በመቋቋም ያስመዘገቡት ውጤት የሚያኮራ ነው ብለዋል። በአትሌቲክስ የተመዘገበው ውጤትና የተገኙ ሜዳሊያዎች ለቀጣይ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። መንግስት ለስፖርቱ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የባህልና የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች በዘጠኝ ስፖርቶች ተሳትፋ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በብስክሌትና ቦክስ ያስመዘገበችው ውጤት በሌሎች ስፖርቶች ላይ ከተሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚያመላክት ነው ብለዋል። ለዚህም መንግስት ከብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አመልክተዋል። በአህጉራዊው ስፖርታዊ ሁነት የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በሚገባ ማስተዋወቅ መቻሉን ተናግረዋል። በአፍሪካ ጨዋታዎች የተመዘገበው ውጤት በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስንቅና አቅም እንደሚሆን ነው አምባሳደር መስፍን የገለጹት።   የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በአፍሪካ ጨዋታዎች ከተመዘገቡ 22 ሜዳሊያዎች 18ቱ በአትሌቲክሱ የተገኘ መሆኑን ገልጻ የተገኘው ውጤት አትሌቶች አስቸጋሪውን የአየር ንብረት ተቋቁመው ያገኙት እንደሆነ ተናግራለች። በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የስፖርት ሁነቶች ላይ በአትሌቲክሱ አመርቂ የሚባል ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅሳለች። እንደ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች በምትሳተፍበት 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክሱ የተሻለ ውጤት ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብላለች። በ13ኛው አፍሪካ ጨዋታዎች በ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች እርምጃ የብር ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ስንታየሁ ማስሬና በ3 ሺህ ሜትር ሴቶች መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ሎሚ ሙለታ በጋና የነበረው ሞቃታማ የአየር ንብረት ፈታኝ ቢሆንም ጫናውን በመቋቋም ሜዳሊያ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮች ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ካገኘቻቸው በተጨማሪም በቦክስ ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ እንዲሁም በብስክሌት አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ኢዜአ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።  
በአፍሪካ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል
Mar 25, 2024 319
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል። የአፍሪካ ጨዋታዎች ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በጋና አክራ መካሄዱ ይታወቃል። በውድድሩ ከ53 ሀገራት የተወጣጡ ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች በ29 የስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል።   ኢትዮጵያም በአምስት የኦሊምፒክ ውድድሮችና አራት ኦሊምፒክ ያልሆኑ ስፖርቶች በድምሩ በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች መሳተፏ ይታወቃል። በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ውሃ ዋና፣ የጠረጴዛና ሜዳ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌትና ወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው የውድድር አይነቶች ናቸው። ኢትዮጵያ በ9 የወርቅ፣ 8 የብር፣ 5 የነሐስ በአጠቃላይ 22 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሁሉም የስፖርት አይነቶች ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 22 ሜዳሊያዎች 18ቱ የተገኙት በአትሌቲክስ ነው፤ 7 የወርቅ 7 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያ በአትሌቲክሱ ተገኝቷል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቦክስ ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ እንዲሁም በብስክሌት አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። በውድድሩ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድንም ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ የሚገባ መሆኑን ኢዜአ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል። ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል ያደርጉለታል ተብሎ ይጠበቃል። በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ግብጽ 101 ወርቅ 46 ብር 42 ነሐስ በድምሩ 189 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በበላይነት አጠናቃለች። ናይጄሪያ በ47 ወርቅ፣ 33 የብር እና 40 የነሐስ በድምሩ 120 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በ32 ወርቅ 32 የብር እና 42 የነሐስ በድምሩ 106 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በውድድሩ ከተሳተፉ 53 ሀገራት 45ቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ሲሆን አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና እና ሞሮኮ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።    
የአደይ አበባ ስታዲየም የምዕራፍ ሁለት ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል
Mar 24, 2024 316
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2016(ኢዜአ)፦የብሔራዊ ስታዲየም (አደይ አበባ ስታዲየም) የምዕራፍ ሁለት ቀሪ የግንባታ ስራ በቅርቡ የሚጀመር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በታህሳስ 2008 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ የብሔራዊ ስታዲየም (አደይ አበባ ስታዲየም) 62 ሺህ ሰዎችን በወንበር የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታም መጠናቀቁ ይታወቃል። አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 50 በመቶ መድረሱንና የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለማከናወን እቅድ ተይዞ ሲሰራ ቆይቷል። የክፍያ ስርዓት ችግርና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለግንባታው መዘገየት ምክንያቶች ሆነው ቆይተዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ልማትና አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አዝመራው ግዛው፤ የብሔራዊ ስታዲየሙን የምዕራፍ ሁለት ቀሪ ግንባታ ለመጀመር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆይታቸውን ገልጸዋል። ይሁንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሚያስፈልጋቸው ስራዎች በቂ ገንዘብ መግኘት አለመቻሉን አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግላቸው ባደረጉት ጥረት የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው የሁለተኛ ምዕራፍ ስፍራዎች ወጪ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ለመሸፈን መስማማቱን ጠቅሰዋል። ለግንባታው ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ ውጤቱ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ጠቅሰው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት የውጭ ምንዛሬ ክፍያና ተጓዳኝ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔውን ሲያሳውቅ የጨረታው ውጤት ይፋ ሆኖ ግንባታው እንደሚጀመር ነው የጠቆሙት። ኤሌክትሮመካኒካል ስራዎችና ስታዲየሙን ጣሪያ የማልበስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚጠይቁ ስራዎች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። የውጭ ምንዛሬ የማይጠይቁና በአገር ውስጥ ተቋራጮች መከናወን የሚችሉ ስራዎች መለየታቸውንም ተናግረዋል። ለዚህም የጨረታ ሰነድ መዘጋጀቱንና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው የገለጹት። የድጋፍ ሰጪ መሰረተ ልማቶች ማጠናቀቂያ ስራዎች፣ የእግረኛ መንገዶች ግንባታና የውጫዊ ገጽታን የማሳመር ስራዎች በአገር ውስጥ ተቋራጮች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል። ለምዕራፍ ሁለት ግንባታ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው ፍጥነት ከተለቀቀ በአገር ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎች ጎን ለጎን በማስኬድ ግንባታውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አመልክተዋል። በምዕራፍ አንድ የስታዲየሙ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውሰው የምዕራፍ ሁለት ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል። የስታዲየሙ ግንባታ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ማስተናገድ በሚችል ደረጃ እየተገነባ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ለብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ እስካሁን ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም አስታውሰዋል። የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር መግጠም፣ የሰው ሰራሽ ሀይቅ ግንባታ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ መግጠም፣ ሳውንድ ሲስተም መዘርጋት፣ የፓርኪንግ ቦታዎች፣ የተጫዋቾች የመለማመጃ ሜዳ እና ሌሎች ስራዎችን በውስጡ አካቷል።
በዞኑ በየዓመቱ የሚዘጋጁ ስፖርታዊ ወድድሮች አካባቢውን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እያገዘ ነው
Mar 21, 2024 204
ጊምቢ፡ መጋብት 12/2016 (ኢዜአ)-- በምዕራብ ወለጋ ዞን በየዓመቱ የሚዘጋጁ ስፖርታዊ ወድድሮች አካባቢውን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እያገዘ መሆኑ ተገለጸ። በዞኑ በ6 የስፖርት ዓይነቶች ለ12 ቀናት የሚቆየው የ2016 ዓ.ም ዓመታዊ ስፖርታዊ ውድድሮች መካሄድ ጀምሯል። በውድድሩ መክፈቻ ላይ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረታ ብርሃኑ እንደገለጹት፤ በውድድሩ 20 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ይሳተፋሉ። ከዚህ በፊት የተካሄዱ ውድድሮች ዞኑን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ማስቻላቸውን ገልጸው የዘንድሮውም ውድድር ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት ይረዳል ብለዋል፡፡   ''ውድድሩ ተወዳዳሪዎች ስፖርታዊ ክህሎታቸውን እንዲያሳዩ ዕድል ይፈጥራል'' ያሉት ሃላፊው፤ በስፖርታዊ ጨዋነት ታግዞ እንዲካሄድ አሳስበዋል። ተሳታፊዎች ስፖርታዊ ውድድሩ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበትና በቀጣይ ሀገርን ለመወከል የሚያስችላችውን እድል የሚያገኙበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በመክፈቻ ወድድርም በጊምቢ ከተማ አስተዳደርና በሖማ ወረዳ መካካል በተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ በአቻ ወጤት ተጠናቋል፡፡ ስፖርታዊ ውድድሮቹ በእግር ኳስ፣ በቅርጫት፣ በእጅ ኳስና በሌሎች እየተካሄዱ እንደሚገኝም ታውቋል።  
ኢትዮጵያ ከሌሴቶ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ታደርጋለች
Mar 21, 2024 219
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሌሴቶ ጋር የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል። የሁለቱ አገራት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለሚደረጉት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾችም ከመጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በአዲስ አበባ ስታዲየምና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ማድረጉንና 26ቱም ተጫዋቾችም በተሟላ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በግብጹ ዜድ ክለብ የሚጫወተው አቤል ያለው ቡድኑን በመቀላቀል የሁለት ቀናት ልምምድ አድርጓል። ተጋጣሚው የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን በ59 ዓመቱ የአገሪቱ የቀድሞ አማካይ ተጫዋች ሌስሊ ኖቲሲ እየተመራ ይገኛል። ብሔራዊ ቡድኑ 23 ተጫዋቾችን ያካተተ ልዑካን ቡድን በመያዝ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምዱን አከናውኗል። ኢትዮጵያና ሌሴቶ የሚያደርጓቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ኢንተርናሽናል ጨዋታነት የተመዘገቡ ሲሆን በገለልተኛ ኢንተርናሽናል ዳኞች እንደሚመራ ፌዴሬሽኑ ገልጿል። ኢትዮጵያ በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 145ኛ፤ ሌሴቶ 148ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያና ሌሴቶ እ.አ.አ በ2022 ባደረጓቸው ሁለት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች በሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው። ዛሬ የሚደረገውን የሁለቱን አገራት ጨዋታ የጅቡቲው መሐመድ ጉዌዲ በዋና ዳኝነት ይመሩታል። የአዲስ አበባ ስታዲየም የእድሳት ስራ ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ ጨዋታው ከሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች በቀር ለተመልካች ዝግ እንደሚሆን ተገልጿል። ኢትዮጵያና ሌሴቶ ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታቸው መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።    
 ካፍ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ላይ እንዲከናወኑ ያስቀመጣቸው ስራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቁ
Mar 20, 2024 397
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት መመዘኛ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ እንዲከናወኑ ያስቀመጣቸው ስራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ። የካፍ ወይም የፊፋ የተቆጣጣሪ ቡድን የስታዲየሙን እድሳት ስራ ለመገምገም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ተገልጿል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ልማትና አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አስማረ ግዛው የስታዲየሙን እድሳት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። የአዲስ አበባ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ባስቀመጠው መመዘኛ መሰረት የእድሳትና የጥገና ስራ መከናወን ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰዋል። በዚህም ካፍ የሰጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በመጀመሪያ ዙር የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ፣ የተፈጥሮ ሳር ንጣፍ፣ የተመልካች መጸዳጃ ቤት፣ የተጫዋቾች የመልበሻ ክፍልና የዳኞች የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕክምና ማዕከል ግንባታ መካሄዱን አመልክተዋል።   በእድሳቱ ሁለተኛ ምዕራፍ የተመልካች መቀመጫ፣ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ክፍል (Media room)፣ የመብራቶች (ፓውዛዎች) እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ስክሪን የመትከል፣ የክብርና ልዩ ክብር እንግዶች ፋሲሊቲዎች እንዲሁም ዘመናዊ የስታዲየም ውሃ ማጠጫ ስርዓት የመዘርጋት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። የምዕራፍ ሁለት እድሳት ከ97 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰው ቀሪ ውስን ስራዎች በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ብለዋል። ከእግር ኳስ ጋር ከተያያዙ የእድሳት ስራዎች በተጨማሪ ነባሩን የአትሌቲክስ መሮጫ መም የመቀየር ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል። የመሮጫ መሙን ለመተካት የአስፋልትና የጠረጋ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውንና አጠቃላይ የመሮጫ ትራክ እድሳት በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለዋል። በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅት በስታዲየሙ ይጀመራል ነው ያሉት። በተያያዘም በምዕራፍ ሶስት የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የበይነ መረብ የቲኬት ሽያጭና በቴክኖሎጂ የታገዘ የደህንነት ስርዓት መዘርጋትን ጨምሮ ሌሎች በስታዲየሙና ዙሪያ ያሉ የውጫዊ ገጽታ ስራዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል። ስራዎቹን ለማከናወን የሚያስችል ጨረታ በቅርቡ እንደሚወጣ የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው የግንባታ ስራው ከሶስት እስከ አራት ወራት ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ መታሰቡን አመልክተዋል። ካፍ በምዕራፍ አንድ እና ሁለት የስታዲየሙ እድሳት መሟላት አለባቸው ያላቸው ስራዎች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል። ካፍ በሁለት ዙር ከሰጣቸው ምክረ ሀሳቦች ውጪ በምዕራፍ ሶስት ከስታዲየሙ ውጪ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ካፍ ባስቀመጣቸው መመዘኛዎች መሰረት ይገነባሉ ብለዋል። የአዲስ አበባ ስታዲየም በመዲናዋ እምብርት ላይ የሚገኝ በመሆኑ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በሶስተኛው ዙር ግንባታ የስታዲየሙን የውጭ ገጽታ የማስዋብ ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል። ለስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ እድሳት 47 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለሁለተኛው ምዕራፍ 190 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አመልክተዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ወይም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የተቆጣጣሪ ቡድን የስታዲየሙ እድሳት ስራ ለመገምገም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት 12 እና 15 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሴቶ ጋር የሚያደርጋቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም