በሴቶች አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለት ሁለተኛ መርሃ ግብር ዛሬ ይደረጋል። 

ቱኒዚያ እና አልጄሪያ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ በፔሬ ጄጎ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቱኒዚያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ በናይጄሪያ 3 ለ 0 ስትሸነፍ አልጄሪያ ቦትስዋናን 1 ለ 0 ረታለች። 

ማሸነፍ ቱኒዚያ በውድድሩ የመቆየት እድሏን እንዲሰፋ ያደርጋል። አልጄሪያ ካሸነፈች ሩብ ፍጻሜ ትገባለች።

የሰሜን አፍሪካ ሀገራቱ ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ ተገናኝተው አልጄሪያ 6 ጊዜ በማሸነፍ ብልጫውን ወስዳለች። ቱኒዚያ 2 ጊዜ ስታሸንፍ 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

አልጄሪያ በጨዋታዎቹ 21 ግቦችን ስታስቆጥር ቱኒዚያ 14 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።  

የምድብ ሁለት ሌላኛው ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም ናይጄሪያ እና ቦትስዋናን ያገናኛል። 

የዘጠኝ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ቱኒዚያን 3 ለ 0 በመርታት ምድቡን እየመራች ነው። 

በአልጄሪያ የ1 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደችው ቦትስዋና ያለ ምንም ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ናይጄሪያ ካሸነፈች ወደ ሩብ ፍጻሜ የሚያስገባትን ትኬት ትቆርጣለች። ቦትስዋና በምድቡ የመጀመሪያ ድሏን ለማስመዝገብ ትጫወታለች።

ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ በ2022 ሞሮኮ ባዘጋጀችው 12ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሶስት ተገናኝተው ናይጄሪያ 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም