በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ዛምቢያ ሴኔጋልን አሸነፈች - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ዛምቢያ ሴኔጋልን አሸነፈች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አንድ ጨዋታ ዛምቢያ ሴኔጋልን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
ማምሻውን በኤል ባቺር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ባርባራ ባንዳ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር ራቼል ኩንዳናንጂ ቀሪዋን ጎል ለዛምቢያ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ንጉዌናር ንዳዬ በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ሁለቱን ግቦች ለሴኔጋል አስቆጥራለች።
ውጤቱን ተከትሎ ዛምቢያ ምድብ አንድን በአራት ነጥብ እየመራች ነው። ሴኔጋል በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
የሴኔጋሏ አጥቂ ንጉዌናር ንዳዬ በውድድሩ ያስቆጠረቻቸውን የግብ ብዛት ወደ አራት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች ነው። የዛምቢያዋ የፊት መስመር ተሰላፊ ባርባራ ባንዳ በሶስት ግቦች ትከተላለች።
በዚሁ ምድብ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአዘጋጇ ሞሮኮ ጋር በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሞሮኮ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛለች።