ፍሉሜኔንሴ እና ቼልሲ ለክለቦች የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ይፋለማሉ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦  በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ፍሉሜኔንሴ እና ቼልሲ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሜትላይፍ ስታዲየም ይካሄዳል።

የብራዚሉ ፍሉሜኔንሴ በሩብ ፍጻሜው የሳዕዲ አረቢያውን አል ሂላልን 2 ለ 1 አሸንፏል።

የእንግሊዙ ቼልሲ የብራዚሉን ፓልሜራስ 2 ለ 1 በመርታት የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብቷል። 

ባለፉት 11 ጨዋታዎችን ሽንፈትን ያላየው ፍሉሜኔንሴ በዓለም ዋንጫው ግምቶችን ፉርሽ በማድረግ ግማሽ ፍጻሜ ደርሷል።

ጠንካራ የተከላካይ ክፍል መስመሩ እና የመልሶ ማጥቃት የአጨዋወት ስልቱ ለተጋጣሚው ራስ ምታት ሆኗል።

በሬናቶ ጋውቼ የሚመራው ፍሉሚኔንሴ በባለፈው የውድድር ዓመት በብራዚል ሴሪ አ ከመውረድ ተርፎ በአጭር ጊዜ እያሳየ ያለው አስገራሚ ብቃት አሰልጣኙን አስወድሷቸዋል። 

የኢንዞ ማሬስካው ቼልሲ በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ በአማካይ ተጫዋቹ የፈጠራ አቅም፣ የታክቲክ ተለዋዋጭነት እና የኳስ የመቆጣጠር አቅም ታግዞ ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል። 

ይሁንና የተከላካይ ክፍል መስመሩ ተጋላጭነት ተጋጣሚዎቹ ግብ እንዲያስቆጥርበት ሲያደርጉ ለመመልከት ተችሏል።

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። 

የእግር ኳስ ልሂቃኑ እና ተመልካቹ ለቼልሲ የማሸነፍ እድሉን በስፋት ቢሰጡም ተጋጣሚው ፍሉሜኔንሴ ያልተጠበቀ ድል ሊያስመዘግብበት እድል አለ የሚሉ አልጠፉም።

ቼልሲ ጨዋታውን ለማሸነፍ ጠንካራውን የብራዚል ክለብ የመከላከል ግድግዳ ማፍረስ ይጠበቅበታል። 

ፍሉሜኔንሴ ጠንካራ የመከላከል ቅርጹን ጠብቆ በሚያገኛቸው አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማስቆጠር የሚያስችል የጨዋታ ስልት ወደ ሜዳ ይዞ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። 

የፍሉሜንሴው ብራዚላዊ የ40 ዓመት አምበል ቲያጎ ሲልቫ የቀድሞ ክለቡን ቼልሲን የሚገጥምበት ጨዋታ መሆኑንም ትኩረት ስቧል። 

የ36 ዓመቱ ፈረተንሳዊ ፍራንስዊ ሌቲክሲየር ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ በፍጻሜው ከፒኤስጂ ወይም ከሪያል ማድሪድ አሸናፊ ጋር ይገናኛል። 

በአሜሪካ አስተጋጅነት እየተካሄደ ያለው የፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ዛሬ 22ኛ ቀኑን ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም