በመዲናዋ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በዛሬው ዕለት በ11 ክፍለ ከተሞች ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው የተገነቡ 122 የስፖርት ማዘውተሪያ እና 1ሺህ 155 የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎችን ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማለዳ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መሪ ሎቄ 40/60 ኮንዶሚኒየም አካባቢና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህፃናት መጫወቻ መሰረተ ልማቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት 15ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ገንብቶ አጠናቋል።
መሰረተ ልማቶቹን ለመገንባት ከወጣው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ 50 በመቶ የሚሆነው በከተማዋ ነዋሪዎች መሸፈኑን ነው የተናገሩት።
አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ3ሺህ 800 በላይ የህፃናት የመጫወቻ ስፍራዎችን መገንባቱንም ገልጸዋል።
ጊዜን፣ እውቀትንና የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማቀናጀት ለህፃናት እና ለወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
ስራዎቹ ህፃናትና ወጣቶች በአካልና በአዕምሮ ብቁ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በስፖርቱ ዘርፍ በዓለምና በአህጉር መድረክ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀን በበኩላቸው፤ በከተማዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአዕምሮና በአካል የዳበረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት ተቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።