የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የሶስተኛ ቀን ውሎ 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሶስት የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ በሆነር ስታዲየም ደቡብ አፍሪካ ከጋና ይጫወታሉ።

ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ2022 በሞሮኮ በተካሄደው 12ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ በፍጻሜው አዘጋጇን ሀገር 2 ለ 1 በመርታት ዋንጫ ማንሳቷ የሚታወስ ነው። 

በተጨማሪም በውድደሩ ተሳትፏቸው ታሪክ አራት ጊዜ ሁለተኛ፣ ሁለት ጊዜ ሶስተኛ እና ሶስት ጊዜ አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ተጋጣሚዋ ጋና በአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሳ በሶስቱም ተሸንፋለች። በውድድሩ ሶስት ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ከዋንጫ መለስ ጠንካራ ተሳትፎ አድርጋለች።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተዋል። ደቡብ አፍሪካ በአራቱ ድል ሲቀናት ጋና ሶስት ጊዜ አሸንፋለች። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

ጋና በጨዋታዎቹ 11 ግቦችን ስታስቆጥር ደቡብ አፍሪካ 10 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች። 

በፊፋ የሴቶች የሀገራት እግር ኳስ ደረጃ ደቡብ አፍሪካ 54ኛ፣ ጋና 66ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በዚሁ ምድብ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ማሊ ከታንዛንያ በቤርካኔ ሙኒሲፓል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ማሊ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። 

እ.አ.አ ሜይ 31 2024 በዳሬሰላም ባደረጉት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

በፊፋ የሴቶች የሀገራት እግር ኳስ ደረጃ ማሊ 78ኛ፣ ታንዛንያ 137ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም