ድራማዊ ክስተቶችን ባስተናገደው አስገራሚ ጨዋታ ፒኤስጂ ባየር ሙኒክን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል - ኢዜአ አማርኛ
ድራማዊ ክስተቶችን ባስተናገደው አስገራሚ ጨዋታ ፒኤስጂ ባየር ሙኒክን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ተጠባቂ መርሃ ግብር ፒኤስጂ ባየር ሙኒክን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በሜርሴዲስ-ቤንዝ ስታዲየም ዴዚሬ ዱዌ በ78ኛው እና ኡስማን ዴምቤሌ በ96ኛው ደቂቃ የማሸነፊያዋን ጎል አስቆጥረዋል።
ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለግብ የቀረቡ በርካታ እድሎች ፈጥረዋል።
የፒኤስጂው ግብ ጠባቂ ጂያንሉዊጂ ዶናሩማ እና የባየር ሙኒክ ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየር ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በአስደናቂ ሁኔታ አድነዋል።
የፒኤስጂ ተከላካዮች ዊሊያን ፓቾ እና ሉካስ ሄርናንዴዝ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።
በጨዋታው ባየር ሙኒክ ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ በመሆናቸው ተሽረዋል። በጨዋታው ማጠናቀቂያ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶም በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ተሽሯል።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ማብቂያ የባየርሙኒኩ የክንፍ ተጫዋች ጀማል ሙሲያላ ከፒኤስጂ ግብ ጂያንሉዊጂ ዶናሩማ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት በግራ እግሩ ቁርጭምጭሚት ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ወጥቷል።
የተጫዋቹ አሰቃቂ ጉዳት በሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች ከፍተኛ ድንጋጤ እና ፍርሃት ፈጥሮ ነበር።
ሙሲያላ ወደ ሆስፒታል በማምራት ህክምናውን እየተከታተለ ይገኛል። ጉዳቱ ተጫዋቹን ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ሊያርቀው ይችላል።
ለ102 ደቂቃዎች የቆየው ጨዋታ አዝናኝ፣ ልብ አንጠልጣይ እና በክስተቶች የተሞላ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ የአውሮፓ ሻምፒዮኑ ፒኤስጂ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል። ቡድኑ ከሪያል ማድሪድ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
የመጨረሻው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በሪያል ማድሪድ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ መካከል ምሽት 5 ሰዓት ላይ በሜትላይፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።