ፒኤስጂ ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል - ኢዜአ አማርኛ
ፒኤስጂ ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ፒኤስጂ ሪያል ማድሪድን 4 ለ 0 በሆነ የሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ትናንት ማምሻውን በሜትላይፍ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፋቢያን ሩዊዝ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኡስማን ዴምቤሌ እና ጎንዛሎ ራሞስ ቀሪዎቹን ጎሎች ለፈረንሳዩ ቡድን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ግቦች የተቆጠሩት የሪያል ማድሪድ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት ነው።
በጨዋታው ፒኤስጂ በጨዋታው በሪያል ማድሪድ ላይ ከፍተኛ ብልጫ የወሰደ ሲሆን ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ይችል ነበር።
የሪያል ማድሪዱ ግብ ጠባቂ ቲቦ ኮርቶዋ ያዳናቸው ያለቀላቸው ኳሶች ቡድኑ በሰፊ ጎል እንዳይሸነፍ አድርጎታል።
ሁለቱ ግቦችን ያስቆጠረው ፋቢያን ሩዊዝ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፒኤስጂ ለፍጻሜ አልፏል። በፍጻሜው ከቼልሲ ጋር ይጫወታል።
የፍጻሜው ጨዋታ እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በሜትላይፍ ስታዲየም ይደረጋል።
የፓሪሱ ክለብ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የክለቦቹ ባስ መንገድ ላይ በገጠመው የትራፊክ መጨናነቅ 10 ደቂቃ ዘግይቶ መጀመሩ አስገራሚ ሆኗል።
ለባለንዶር ሽልማት የታጨው ኡስማን ዴምቤሌ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 35 ከፍ አድርጓል።
ሪያል ማድሪድ ዓመቱን ያለ ዋንጫ አጠናቋል።