የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ በምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ይመለሳል።

በምድብ አንድ ሴኔጋል ከዛምቢያ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በኤል ባቺር ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሴኔጋል በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ምድቡን በሶስት ነጥብ እየመራች ነው። 

የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈች ሴኔጋል ለሩብ ፍጻሜ ታልፋለች።

በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከአዘጋጇ ሞሮኮ ጋር ሁለት አቻ የተለያየችው ዛምቢያ በውድድሩ ለመቆየት ማሸነፍ ግድ ይላታል።


 

ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ ሞሮኮ ባሰናዳችው 12ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ተገናኝተው ነበር። 

በመደበኛ 90 ደቂቃ አንድ አቻ ተለያይተው ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቶ ዛምቢያ በመለያ ምት 4 ለ 2 አሸንፋ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች። 

በዚሁ ምድብ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአዘጋጇ ሞሮኮ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ዴሞክራቲክ ኮንጎ ያለ ምንም ነጥብ ሶስተኛ፣ ሞሮኮ በአንድ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። ማሸነፍ ሀገራቱ ወደ ሩብ ፍጻሜ የመግባታቸውን እድል ያሰፋል። 

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሁለት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች ተገናኝተው ሞሮኮ በሁለቱም አጋጣሚ አሸንፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም