አዘጋጅ ሀገር ሞሮኮ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች - ኢዜአ አማርኛ
አዘጋጅ ሀገር ሞሮኮ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አንድ መርሃ ግብር ሞሮኮ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 4 ለ 2 አሸንፋለች።
ትናንት ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አምበሏ ጊዝላኔ ቼባክ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች።
በውድድሩ ሀትሪክ የሰራች የመጀመሪያ ተጫዋች ሆናለች። በውድድሩ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ አራት ከፍ አድርጋለች።
ያስሚን ምራቤት ለሞሮኮ ቀሪዋን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥራለች።
ሜርቬል ናንጉጂ እና ፍላቪን ማዌቴ ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ሞሮኮ በጨዋታው በኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ብልጫ የወሰደች ሲሆን የተሻለ የግብ እድልም ፈጥራለች።
ውጤቱን ተከትሎ አዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች። በአራት ነጥብ ደረጃዋን ከሶስተኛ ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጋለች።
በምድቡ ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻው አራተኛ ደረጃ ያዛለች።
በዚሁ ምድብ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ ዛምቢያ ሴኔጋልን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
ዛምቢያ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞሮኮ ከሴኔጋል የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታዎች ናቸው።