በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
በምድብ አንድ ሴኔጋል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በኤል ባቺር ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ዶሜክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ ቀሪውን ጨዋታ ሴኔጋል አሸንፋለች።
በፊፋ የሴቶች የሀገራት እግር ኳስ ደረጃ ሴኔጋል 81ኛ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 109ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በዚሁ ምድብ ትናንት በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ሞሮኮ እና ዛምቢያ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
የአፍሪካ ዋንጫን ዘጠኝ ጊዜ በማንሳት የውድድሩ ቁንጮ ሀገር የሆነችው ናይጄሪያ ከቱኒዚያ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሁለቱ የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ተቀናቃኝ ሀገራት እስከ አሁን ዘጠኝ ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተዋል።
ናይጄሪያ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ቱኒዚያ ሁለት ጊዜ አሸንፋለች። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በዘጠኙ ጨዋታዎች ናይጄሪያ 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ፣ ቱኒዚያ 9 ጎሎችን አስቆጥራለች።
በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛ የበላይነት ያላት ናይጄሪያ ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች።
በፊፋ የሴቶች የሀገራት እግር ኳስ ደረጃ ናይጄሪያ 36ኛ፣ ቱኒዚያ 89ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በዚሁ ምድብ ምሽት 4 ሰዓት ላይ አልጄሪያ ከቦትስዋና በፔሬ ጄጎ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ሀገራት በውድድር ጨዋታዎች ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ያደረጓቸውን ሶስት ጨዋታዎች አልጄሪያ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች።
አልጄሪያ በጨዋታዎቹ 10 ግቦችን ስታስቆጥር ቦትስዋን ማግባት የቻለቸው አንድ ጎል ብቻ ነው።
ጨዋታው አልጄሪያ በቦትስዋና ላይ ያላትን የበላይነት ለማስቀጠል፣ ቦትስዋን በተጋጣሚዋ ላይ የመጀመሪያ ድሏን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።
በፊፋ የሴቶች የሀገራት እግር ኳስ ደረጃ አልጄሪያ 82ኛ፣ ቦትስዋና 153ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።