“ ከፍጻሜው በፊት የፍጻሜ ጨዋታ” የተባለው የፒኤስጂ እና ሪያል ማድሪድ ፍልሚያ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦  በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ፒኤስጂ እና ሪያል ማድሪድ ዛሬ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል። 

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሜትላይፍ ስታዲየም ይካሄዳል።

ፒኤስጂ በሩብ ፍጻሜው ባየር ሙኒክን 2 ለ 0 አሸንፏል። ቡድኑ ሁለት ተጫዋች በቀይ ወጥቶበት ያስመዘገበው ውጤት አድናቆት አስችሮታል። 

ተጋጣሚው ሪያል ማድሪድ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን በሩብ ፍጻሜው 3 ለ 2 በማሸነፍ አራት ውስጥ ገብቷል። ማድሪድ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተቆጠሩበት ግቦች ስጋት ውስጥ ከተውት ነበር። 

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፒኤስጂ በሉዊስ ኤነሪኬ እየተመራ በዘንድሮው የውድድር አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።

የፈረንሳይ ሊግ እና የፈረንሳይ ጥሎ ማለፍን ክብር በእጁ ያስገባው የፓሪሱ ክለብ የአውሮፓውን ቁንጮ ውድድር አሸንፏል።

ድንቁን ዓመት የዓለም እግር ኳስ ትልቁን ክብር በማሸነፍ የመደምደም ህልም አለው።

የ15 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ ያለ ዋንጫ ያጠነቀቀ ሲሆን አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ቡድኑ ከተረከቡት በኋላ ጥሩ መሻሻል አሳይቷል። 

የአማካይ ክፍል የኳስ ቁጥጥር እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከክንፍ መስመር ተጫዋቾች ፈጣን እንቅሰቃሴ ጋር ተጣሮ ሎስ ብላንኮሶቹን ጥንካሬውን መልሶ እንዲያገኝ እያደረጉት ነው።

ሁለቱ የአውሮፓ ኃያላን እስከ አሁን በውድድር ጨዋታዎች 13 ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ 6 ጊዜ ሲያሸንፍ ፒኤስጂ 3 ጊዜ ድል ቀንቶል ። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በዛሬው ጨዋታ በሩብ ፍጻሜው ወሊያን ፓቾ እና ቲኦ ሄርናንዴዝን  በቀይ ካርድ ያጣው ፒኤስጂ ተከላካዩ ላይ መጠነኛ መሳሳት ሊያጋጥመው ይችላል።

ለባለንዶር የታጨው ኡስማን ኤምቤሌ ወደ ሙሉ የአካል ብቃት እና የጨዋታ ዝግጁነት መመለሱ ለፈረንሳዩ ቡድን መልካም  ዜና ነው። 

ተጋጣሚው ሪያል ማድሪድ በሩብ ፍጻሜ ቀይ ካርድ ያየውን ዲን ሀውሰን አገልግሎት የማያገኝ ሲሆን በሱ ምትክ ራኡል አሴንሲዮ እና ኤደር ሚሊታኦ ሊሰለፉ ይችላሉ የሚሉ ግምቶች እየወጡ ነው።

የኪሊያን ምባፔ ወደ መመለስ ለነጮቹ የምስራች የሆነላቸው ሲሆን አጥቂው ከዓመት በፊት በነጻ ዝውውር የለቀቀውን የቀድሞ ቡድኑን ይገጥማል። 

በአማካይ ክፍሉ ቪቲንሃ፣ ጆአ ኔቬስ እና ፋቢያን ሩዊዝ ከፒኤስጂ፣ ጁድ ቤሊንግሃም፣ ፌዴሪኮ ቫልቬርዶ እና አርዳ ጉለር ከሪያል ማድሪድ የሚኖራቸው ፍጥጫ የበለጠ አጓጊ ሆኗል።

እጅግ ጠንካራ እና ተቀራራቢ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ በሚጠበቀው ጨዋታ ፒኤስጂ በጠበበ ሁኔታም ቢሆን ሊያሸንፍ ይችላል የሚሉ ግምቶች እየወጡ ነው።

የ44 ዓመቱ ፖላንዳዊ ሲሞን ማርሲኒያክ ተጠባቂውም ፍልሚያ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ በፍጻሜው ከቼልሲ ጋር ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም