ሪያል ማድሪድ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል - ኢዜአ አማርኛ
ሪያል ማድሪድ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 3 ለ 2 አሸንፏል።
ትናንት ማምሻውን በሜትላይፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጎንዛሎ ጋርሺያ፣ ፍራንሲስኮ ጋርሺያ እና ኪሊያን እምባፔ የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ማክሲሚሊያን ቤየር በጨዋታ እና ሴርሁ ጉይራሲ በፍጹም ቅጣት ምት ለቦሩሲያ ዶርትሙንድ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
የሪያል ማድሪድ ተከላካይ ዲን ሀውሰን በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በጨዋታው ሪያል ማድሪድ በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው የተሻለ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ ሪያል ማድሪድ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል። ለፍጻሜ ለማለፍ ከፒኤስጂ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ወጣቱ አጥቂ ጎንዛሎ ጋርሺያ በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ አራት ከፍ አድርጓል።
ጋርሺያ ከውድድሩ ከተሰናበቱት የአል ሂላሉ ማርኮስ ሌኦናርዶ እና የቤኔፊካው አንጌል ዲ ማሪያ ጋር በግብ ተስተካክሏል።
ታዳጊው አጥቂ ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥሮ ኮከብ ግብ አግቢ የመሆን እድል አለው።
ትናንት በተደረገው ሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ፒኤስጂ ባየር ሙኒክን 2 ለ 0 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በፍሉሜኔንሴ እና ቼልሲ መካከል ይደረጋል።
የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳሉ።