ቀጥታ፡

ሊቨርፑል እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ አቻ ተለያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ሊቨርፑል እና ቶተንሃም ሆትስፐርስን ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።

ማምሻውን በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ዶምኒክ ስቦዝላይ በ18ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ በቅጣት ምት ያስቆጠረው ግብ ቀያዮቹን መሪ አድርጓል።

ሪቻርልሰን በ90ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፈው ጎል ቶተንሃም አንድ ነጥብ አግኝቷል።

 

በጨዋታው ሊቨርፑል የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም ቶተንሃም ግልጽ የግብ እድሎችን በመፍጠር ተሽሎ ተገኝቷል።

ሊቨርፑል በ49 ነጥብ ደረጃውን ከስድስተኛ ወደ አምሰተኛ ከፍ አድርጓል።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ጥሏል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ30 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል።

የመውረድ አደጋ ውስጥ ያለበት ቶተንሃም ባለፉት 12 የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ዛሬ ቀን ላይ በተደረጉ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ አስቶንቪላን 3 ለ 1 አሸንፏል።

ክሪስታል ፓላስ ከሊድስ ዩናይትድ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከፉልሃም ያደረጉት ጨዋታ በተመሳሳይ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የ30ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ነገ ብሬንትፎርድ ከዎልቭስ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም